የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ቀሪ ስራዎች ስኬታማነት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድጋፋቸውን ማጠናከር አለባቸው-ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ቀሪ ስራዎች ስኬታማነት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ድጋፋቸውን ማጠናከር አለባቸው-ባለስልጣኑ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2018 (ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ቀሪ ስራዎች ስኬታማነት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ማጠናከር እንዳለባቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ገለጸ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የካቲት 11 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽንን የሥራ ዘመን ለስምንት ወራት ማራዘሙ ይታወቃል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች የህዝብን እና የሀገርን ተጠቃሚነት በሚያረጋግጡ ሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የነቃ ተሳትፎ እያደረጉ ይገኛል ብለዋል።
ድርጅቶች በንቃት እየተሳተፉ ካሉባቸው ሀገራዊ አጀንዳዎች መካከል እንደ ሀገር ለዘመናት የተሻገሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት እየተከናወነ ባለው የሀገራዊ ምክክር እንቅስቃሴ ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም ኮሚሽኑ ሀገራዊ ምክክርን ለማድረግ እስካሁን ባለፈባቸው ሂደቶች ላይ ሚናቸው የጎላ እንደነበረ አንስተዋል።
በተጨማሪም ባለፈ ስለ ሀገራዊ ምክክር ህብረተሰቡ ያላቸውን ንቃተ ህሊና እንዲያሳድጉ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራም እንደዚሁ ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ቀሪ ስራዎች ስኬታማነት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እያበረከቱ ያለውን አስተዋጽኦ አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።
ለሀገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ያላቸውን ሚና መወጣት እንዲችሉ ባለስልጣኑ የሚጠበቅበትን ሚና ለመጫወት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል።