ቀጥታ፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ባህል ማድረግ ይገባል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2018 (ኢዜአ)፦ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ህብረተሰቡ የአካል ብቃት  እንቅስቃሴን ባህል ሊያደርግ እንደሚገባ  የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ ገለጹ።

ጤና ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማትና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን "ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን እንከላከል!በጊዜ እንመርመር እንታከም! ጤናችንን እንጠብቅ!" በሚል መሪ ሀሳብ ወርሃዊ የስፖርት እንቅስቃሴን በአዲስ አበባ አካሂዷል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ የጤና ምርመራዎችና እና አውደ ራዕይ ተካሂዷል።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጄ ዱጉማ በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ ዘውትር የአካል ብቃት እንቅስቃሴን በማድረግ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠር ይቻላል።

የደም ግፊት፣ ስኳርና ካንሰር  እንዲሁም የአንጎል  ህመሞችን እና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ስርጭት ለመግታት  ከጤና ፖሊሲዎች ጋር  በማጣጣም በርካታ  ስራዎች እየተሰራ መሆኑን  ተናግረዋል።

ዜጎች ስለ አካል ብቃት እንቅስቃሴና የአኗናር ዘይቤያቸውን በመቀየር በሽታዎችን መከላከልና መቆጣጠር እንዲችሉ በተለያዩ መድረኮች ግንዛቤዎች እየተሰጡ መሆኑን  ገልጸዋል።

ተቋማዊ ወርሃዊ  የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር እየተደረገ መሆኑን ጠቅስው፤ ይህም የትብብርና የአንድነትን መንፈስ ማጎልበት እንደሚያስችል ተናግረዋል።


 

በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው ወርሃዊ  የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በቀጣይ በሁሉም የአገሪቱ ክልሎች እና በጤና ተቋማት እንደሚስፋፋ ገልጸዋል።

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ህብረተሰቡ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ባህል ማጎልበት አለበት ብለዋል።

በዛሬው ዕለት በተካሄደው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል፤ ወይዘሮ ታከለች ሞገስ እና መሐመድ ተማም በበኩላቸው ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ጤናማ አመጋገብና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ወሳኝ ናቸው  ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ በኮሪደር ልማቱ የተገነቡ የመሰረተ ልማት ስራዎችና አረንጓዴ ስፍራዎች ለአካል ብቃት እንቅስቃሴና ለእግር ጉዞ ምቹ በመሆናቸው ዜጎች ምቹ ሁኔታዎቹን በመጠቀም ጤናቸውን ሊጠብቁ እንደሚገባም ገልጸዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም