ቀጥታ፡

በክህሎትና ስነምግባር የታነፀ ትውልድ የማፍራቱ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል -ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2018 (ኢዜአ)፦ በክህሎት፣ በእውቀትና በስነምግባር የታነፀ ትውልድ ለማፍራት የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል ገለፁ።

የኢፌዴሪ ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት በቦሌ አራብሳ አካባቢ ያስገነባውን የቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤት ምረቃ እና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የግንባታ ማስጀመሪያ መርሀግብር አካሂዷል።


 

የስራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪሃት ካሚል በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ በክህሎት የዳበሩ ህፃናትና ታዳጊዎችን ለማፍራት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ዛሬ የተመረቀው የማህበረሰብ አቀፍ ትምህርት ቤት በክህሎት በእውቀትና በስነምግባር የታነጸ ትውልድን ለማፍራት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ገልፀዋል።

በክህሎትና በእውቀት የዳበረ ትውልድ የማፍራት ሀላፊነታችንን ሁላችንም ልንወጣ ይገባልም ብለዋል።


 

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ በበኩላቸው፤ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን በርካታ ስራ እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በትምህርትና ስልጠና ዜጎችን ወደ ላቀ እውቀት ለማሸጋገር በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አክለዋል።

የኢፌድሪ ቴክኒክና ሙያ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ብሩክ ከድር(ዶ/ር) ዛሬ የተመረቀው ትምህርት ቤት ችግር ፈቺ የሆኑ ዜጎችን ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።


 

ትምህርት ቤቱ ታዳጊዎች በክህሎት የዳበረ እውቀት እንዲጨብጡ ለማስቻል ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል።

መሰል ሞዴል ትምህርት ቤት መቋቋሙ ለሙያ ትምህርት የሚሰጠውን የተዛባ አስተሳሰብ ለማስተካከል ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም