አይቻልምን የሰበሩ የሰማይ ከዋክብት - ኢዜአ አማርኛ
አይቻልምን የሰበሩ የሰማይ ከዋክብት
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ወደ ሀገር ውስጥና ውጭ ሀገራት በሴቶች ብቻ የሚመሩ ስምንት በረራዎችን ያደርጋል።
ዓለም ዙሪያ ካሉ የንግድ አውሮፕላን አብራሪዎች መካከል የሴቶች ድርሻ እስከ ስድስት በመቶ የሚደርስ ብቻ መሆኑን መረጃዎች ያመላክታሉ።
ከዓለም አቀፉ አማካኝ የተሻለ ቁጥር ከያዙት መካከል የህንድ አየር መንገድ ኤር ኢንዲያ ከጠቅላላ አብራሪዎቻቸው ውስጥ እስከ 15 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድም አሁን ላይ 95 ሴት አብራሪዎች ያሉት ሲሆን፣ ቁጥሩን በፍጥነት እያሳደጉ ካሉ ጥቂት የአፍሪካ አየር መንገዶች በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው።
ኢዜአ ያነጋገራቸው በበረራው የተሳተፉ ሴት ረዳት አብራሪዎች በሴቶች ብቻ በሚመራ በረራ መሳተፍ ኩራትም ደስታም የሚፈጥር መሆኑን ይገልፃሉ።
ረዳት አብራሪ ፅዮን ደመቀ እንዳሉት በኢትዮጵያ የመጀመሪያዋ ወጣት ሴት አውሮፕላን አብራሪ ካፒቴን አምሳለ ጓሉን በማየትና በመነሳሳት ዘርፉን ተቀላቅለዋል።
ዘርፉን ከተቀላቀሉ ወዲህ በሚሄዱባቸው ቦታዎች ሁሉ የሚመለከቷቸው ሰዎች ማበረታቻ እንደሚሰጧቸውም ተናግረዋል።
ሌላዋ ረዳት አብራሪ ሊዲያ ጋሜ በበኩላቸው ዘርፉ ለሴት ልጅ ይፈትናሉ ተብለው ከሚታሰቡ መካከል ቢሆንም ሴት ልጅ እንደምትችል ካሳዩ ቀደምቶቻችን በመማር ዘርፉን ተቀላቅለናል ብለዋል።
በሴቶች ብቻ በተመራ በረራ ላይ ተሳታፊ መሆናቸው ደስታና ኩራትን ያጎናፀፋቸው መሆኑንም ረዳት አብራሪዎቹ ገልፀዋል።
በትጋት ጠንክሮ በመስራት የሚኖሩ ችግሮችን በድልና በተስፋ ማለፍ የስኬት ቁልፍ ነው ያሉት አብራሪዎቹ ሴቶች የአልችልምን መንፈስ ሰብረው የራስ መተማመንን ካጎለበቱ የፈለጉት ቦታ ይደርሳሉ ሲሉም ገልጸዋል።