ቀጥታ፡

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ የሚያስችለንን የመራጭነት ካርድ በመውሰድ ድምጻችንን ለመስጠት ተዘጋጅተናል-ነዋሪዎች

ነጌሌ ቦረና ፤የካቲት 29/2018 (ኢዜአ)፡- በ7ኛው ጠቅላላ  ምርጫ መሳተፍ የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ በመውሰድ ድምጻቸውን ለመስጠት ከወዲሁ መዘጋጀታቸውን በምስራቅ ቦረና ዞን የነጌሌ ቦረና ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባሰቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ከትናንት የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በየምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ መጀመሩ ይታወሳል።

በዚሁ መርሃ ግብር መሰረት ኢዜአ በነጌሌ ቦረና ከተማ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ካርድ ሲወስዱ ያገኛቸውን ነዋሪዎች አነጋግሯል።

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል  አቶ ጉራቻ ጃተኒ በሰጡት አስተያየት በመጪው ግንቦት በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ ከወዲሁ ተዘጋጅተዋል።

ለዚህም የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን ጠቅሰው ድምጻቸውንም ለሀገር ልማትና እድገት ይሰራል ብለው ላመኑበት ፓርቲ  እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

የጎቢቻ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ቱራ ሊበን በበኩላቸው በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በመሳተፍ የዜግነትና ህገ መንግስታዊ መብታቸውን ለመጠቀም የመራጭነት ካርድ እንደወሰዱ ተናግረዋል።

ምርጫ የሀገረ መንግሥት ግንባታን ለማጽናት ወሳኝ በመሆኑ እዚህ ላይ አተኩሮ ለሚሰራ ፓርቲ ድምጼን እሰጣለሁ ብለዋል።

ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የአከባቢያቸውን ሠላም ነቅተው በመጠበቅ  የበኩላቸውን  ድርሻ እንደሚወጡም አስታውቀዋል።

ሌላኛው የመራጭነት ካርድ መውሰዱን የሚናገረው የከተማው ነዋሪ ወጣት ማሙሽ ፈይሳ በተለያዩ የሚዲያ አማራጮች የሚተላለፈውን የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር በአግባቡ በመከታተል ለሚደግፈው ፓርቲ ድምጹን ለመስጠት መዘጋጀቱን አስታውቋል።

ክርክሩ የመራጭነት ካርድ ለመውሰድና በምርጫው ለመሳተፍና ድምጽ ለመስጠት እንዳነሳሳውም አክሏል።

የነገሌ ምርጫ ክልል አስተባባሪ አቶ አባይነህ ወርቁ በዞኑና በነጌሌ ቦረና ከተማ በሚገኙ ሁሉም ምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ በሰላማዊ መንገድ እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል።

የመራጮች የምዝገባ ሂደቱንም 167 የምርጫ አስተባባሪዎች በቅርበት እየተከታተሉት ሲሆን 668 ምርጫ አስፈጻሚዎችም ምዝገባውን እያስፈጸሙ እንደሚገኙ አስታውቀዋል።።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም