ቀጥታ፡

ብሔራዊ ጥቅምን ለታሪካዊ ጠላቶች አሳልፎ ለመስጠት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ባለድርሻ አካል ሊሆኑ አይገባም - በለጠ ሞላ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2018 (ኢዜአ)፦ ብሔራዊ ጥቅምን ለታሪካዊ ጠላቶች አሳልፎ ለመስጠት የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ አውድ ውስጥ ባለድርሻ አካል ሊሆኑ እንደማይገባ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ ሊቀ መንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ ሊቀመንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በወቅታዊ ጉዳዮች፣ በቀይ ባህርና የባህር በር ጥያቄ፣ ምርጫ 2018 በተመለከተና በሌሎች ጉዳዮች ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገው ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ቀይ ባህር ያለ ኢትዮጵያ ህዝብ ፈቃድና ይሁንታ በፖለቲካ ሴራ ያጣነው የተፈጥሮ ሃብታችን ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት ጥያቄ ተፈጥሯዊ፣ ህጋዊ እና መልክዓምድራዊ መብቷን መሰረት ያደረገ ሲሆን፣ ይህንን ታሪካዊ ሀብት ማጣት በአሁኑ ትውልድ ዘንድ ከፍተኛ የቁጭት ስሜት ፈጥሯል።

መንግስት ይህንን የህዝብ ጥያቄ ለመመለስና ኢትዮጵያ ያላትን ስትራቴጂካዊ ጥቅም ለማስከበር የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ስልቶችን በመከተል ረጅም ርቀት ተጉዟል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ሊቀ መንበር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ለኢትዮጵያ የዓባይ ውሃና ቀይ ባህር ስትራቴጂካዊ ጥቅሞቿ ናቸው።

ኢትዮጵያ የቀይ ባህርን ምንም ዓይነት ህጋዊ መሰረት በሌለው አግባብ በሴራ እንድታጣው መደረጉን አንስተው፤ ይህ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመ ታላቅ በደል ነው ብለዋል።

ከዚህ አኳያ መንግስት የባህር በር ጥያቄን ሀገራዊ አጀንዳ አድርጎ ማምጣቱን አብን በአዎንታ የሚቀበለውና የሚደግፈው አካሄድ መሆኑንም ገልጸዋል።

በወቅቱ በድፍረት የተወሰነ የፖለቲካ ውሳኔ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመ ታሪካዊ በደልና የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፎ የሰጠ ታሪካዊ ስህተት እንደሆነም አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ በታሪክና በተፈጥሮ ያላትን የባህር በር የማግኘት መብት ዳግም የሚያረጋግጥላት ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚገባ የገለጹት ሊቀመንበሩ፤ አብንም ይህንን ፍትሃዊ ጥያቄ ከግብ ለማድረስ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ስለሆነም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለታሪካዊ ጠላቶች አሳልፈው ለመስጠት የሚሰሩ የፖለቲካ ኃይሎች በፖለቲካው አውድ ውስጥ ባለድርሻ አካል መሆን እንደሌለባቸው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ የዓባይ ውሃ ለኤሌትሪክ ሃይል ማመንጫነት በመገደብ ተጠቃሚነቷን በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ማረጋገጧን አንስተው፤ የባህር በር ጥያቄ ላይም በጋራ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።

ታሪካዊ ጠላቶች ኢትዮጵያ የልማት ጥረቶቿ እንዲደናቀፉ ሌት ተቀን እንደሚሰሩ ያመለከቱት ሊቀ መንበሩ፤ ኢትዮጵያውያን ግን የጋራ ጠላቶቻቸውን ሴራ በፅናት የመከቱበት ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

አሁን ላይ ከእነዚህ የብሔራዊ ጥቅም ጉዳዮች በላይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ሌላ ምንም ዓይነት አጀንዳ እንደሌለ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም