ቀጥታ፡

መንግሥት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነ ነው

ጅግጅጋ፣ የካቲት 29/2018(ኢዜአ)፦ መንግሥት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነ መሆኑን የሶማሌ ክልል የሴቶች እና ህጻናት ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኡበህ አብዱረህማን ተናገሩ።

ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን (ማርች 8) "50ኛ ዓመት የሴቶች ድምፅ ለእኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሃሳብ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ተከበረ።


 

የሶማሌ ክልል የሴቶች እና ህጻናት ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ሃላፊ ኡበህ አብዱረህማን እንደገለጹት፣ መንግሥት የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት እያከናወነ ነው።

የሴቶችን ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተሠሩ ሥራዎች አበረታች ለውጦች መገኘታቸውንም ነው የተናገሩት።

በሶማሌ ክልል ሴቶችን ለአመራርነትና ውሳኔ ሰጪነት በማብቃት በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ የላቀ ተሳትፎ እንዲኖራቸው የተለያዩ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

ባለፉት አመታት የተገኙትን የሴቶች ተሳትፎ የሚያጠናክሩ ስኬቶች ማስቀጠልና ማጎልበት እንደሚገባም ተናግረዋል።

ያለ ሴቶች ንቁ ተሳትፎ ኢትዮጵያ ያቀደችውን የብልጽግና ጉዞ ለማረጋገጥ  የማይታሰብ መሆኑን አንስተው በዚህ ረገድ ጠንካራ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።



ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል ዘሀራ ዩሱፍ ሴቶች የቤተሰብና የህብረተሰብ ምሰሶ እንደሆኑ ተናግረው እናቶች አምራች ትውልድ በማፍራት የሀገር ባለውለታ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ሴቶች መንግሥት እያከናወነ ያለውን ልማት  በመደገፍ የድርሻቸውን እንዲወጡ ለይላ ሂስ አህመድ ጠየቀዋል፡፡


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም