ቀጥታ፡

የሥርዓተ ጾታ እኩልነትንና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2018(ኢዜአ)፦ የሥርዓተ ጾታ እኩልነትንና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ ወደ ሀገር ውስጥና ውጭ ሀገራት በሴቶች ብቻ የሚመሩ ስምንት በረራዎች እንደሚከናወን አስታውቋል፡፡


 

ሚኒስትሯ ይህንን የገለጹት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን (ማርች 😎 ምክንያት በማድረግ በሴቶች ብቻ ለሚመራው የበረራ ቡድን በስካይላይት ሆቴል በተዘጋጀው የሽኝት መርሃ ግብር ላይ ነው።

አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ115ኛ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በማስመልከት በሴቶች የሚመሩ ስምንት በረራዎችን ያደርጋል።

በዚህ ወቅት የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ አየር መንገዱ የኢትዮጵያ ኩራት በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገርን ስም ከማስጠራት ባለፈ፣ ሴቶችን በማብቃት ረገድ አርዓያነት ያለው ተግባር እያከናወነ ይገኛል።


 

አየር መንገዱ የጾታ እኩልነትን፣ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሴቶችን ለማብቃትና እኩል ዕድል ለመፍጠር የግሉ ዘርፍም የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

መንግስት ሴቶች ሙሉ አቅማቸውን እንዲያወጡ የሚያስችል ምቹ ሁኔታን እየፈጠረ መሆኑን ጠቁመው፤ የስርዓተ ፆታ እኩልነትና የሴቶችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ ብለዋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ተቋም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጃኔት ኪም በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሴቶች ብቻ የተመራ በረራ ማድረጉ ሴቶች ዕድሉ ከተሰጣቸው የማይወጡት አቅም እንደሌለ ማሳያ ነው ብለዋል።


 

አየር መንገዱ በአቪዬሽን ዘርፍ እያከናወነ ካለው የላቀ ተግባር በተጨማሪ ሴቶችን በዘርፉ ለማብቃት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም የእኩልነት መርህን በተግባር ለዓለም ያሳየ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው፤ የበረራ መርሃ ግብሩ ከፓይለት እስከ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪነት ያለውን ሂደት ጨምሮ ሙሉ በሙሉ በሴቶች የሚመራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

አየር መንገዱ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት በተመረጡ ሀገራት በሴቶች ብቻ የተመራ በረራ ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሰው፤ ዘንድሮም ወደ ሀገር ውስጥና ውጭ ሀገራት ስምንት በረራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የአየር መንገዱ 40 በመቶ ሰራተኞች እንዲሁም 35 በመቶ አመራሮች ሴቶች ሲሆኑ የሴት ፓይለቶች ቁጥርም 95 ደርሷል።

ይህ የበረራ መርሃ ግብር ሴቶች በአቪዬሽን ዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎ ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም