ቀጥታ፡

የትግራይ ሕዝብ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ተጠቃሚነት ትብብሩን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል -ምሁራን

ቦንጋ፤ የካቲት 29/2018(ኢዜአ)፦ የትግራይ ክልል ሕዝብ ለዘላቂ ሰላምና ልማት ተጠቃሚነት ትብብሩን አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ሲሉ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በትግርኛ ቋንቋ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ የትግራይ ህዝብ በሀገር ደረጃ እየተመዘገበ ካለው ሁሉን አቀፍ ልማትና ሰላም ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባው መግለፃቸው ይታወቃል።

ለክልሉ ህዝብ ሁለንተናዊ ልማትና ተጠቃሚነት መንግስት ቁርጠኛ አቋም ይዞ እየሰራ መሆኑን አንስተው የህወሃት ቡድን ለሌላ ጦርነት እየሰራ ስለመሆኑ ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግኑኝነት ትምህርት ክፍል መምህር ረዳት ፕሮፌሰር ያሬድ አያሌው (ዶ/ር)፣ የተራማጅነት እሳቤ የሌለው የህወሃት ቡድን ዘመኑን ለሚመጥን የፖለቲካ እሳቤ ዝግጁነት የሌለው መሆኑን ባለፉት ዓመታት ማየት ተችሏል ብለዋል።

ይህም በመሆኑ በተለይም የትግራይ ክልልና ህዝቡ የለውጡ ተጠቃሚ እንዳይሆን መሰናክል ሆኗል ሲሉ ጠቅሰዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ መንግስት የትግራይ ሕዝብ የሰላምና የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ያለውን የጸና አቋም የገለጹበት መሆኑን አንስተው፣ የህወሃት ቡድን ከዚህ በተቃራኒ ቆሞ እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በመሆኑም የህወሃትን ቡድን ያረጀ አስተሳሰብ ለመቀየር በተለይም የክልሉ ህዝብ ከፍተኛ ተነሳሽነት ወስዶ መንቀሳቀስ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል።

የህወሃት ቡድን የትግራይን ሕዝብ በተለይም ወጣቱን ሀይል እንደማሲያዣ በመጠቀም አሁን እንደሀገር እየተመዘገበ ካለው የልማት፣ የሰላምና የአንድነት ጉዞ ተነጥሎ እንዲኖር እያደረገው መሆኑን በአግባቡ በመረዳት የጥፋት ቡድኑን በቃ ሊለው ይገባል ብለዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ መንግስት የትግራይ ሕዝብ ወደ ሰላሙ እንዲመለስ እና የልማቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ያሳያል ያሉት ዶክተር ያሬድ ፤ ህዝቡም የመንግስትን ጥረት ደግፎ ለለውጥ መስራት ይጠበቅበታል ሲሉ ተናግረዋል።

የትግራይ ህዝብ የህወሃትን ቡድን እኩይ ዓላማ ማክሸፍ የሚችለው ጠንካራ ትብብርና ፅኑ ትግል ማድረግ እንዳለበት ጠቁመው፤ ይህንን ለማድረግ ጊዜ ማባከን አይገባም ብለዋል።


 

በዲላ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ አዲሱ ፍሪንጆ (ዶ/ር) ፤ እንዳሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በክልሉ ተፈጥሮ የነበረውን የሰላም እጦት ምክንያት ለይተው ለዘላቂ ሰላም ጠቃሚ ናቸው ያሏቸውን ሃሳቦች ማንሳታቸው ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

የትኛውም የፖለቲካ አስተሳስብ ከዘመኑ ጋር ተራማጅ መሆኑን ያነሱት ምሁሩ፣ የህወሃት ቡድን ተቀባይነት በሌለውና በቆየ አስተሳሰብ ዛሬም እቀጥላለሁ ማለቱ የማይለወጥና ቆሞ ቀርነቱን ያሳያል ብለዋል።

ባረጀ አስተሳሰቡ ቀደም ሲል በፈጠረው ግጭት የትግራይ ክልል ህዝብ ከልማት እንዳይጠቀም ማደረጉን አስታውሰው፣ ሰላም ወዳዱ የትግራይ ህዝብ በተለይ ወጣቱ ቡድኑን ሌላ ግጭት አንፈልግም ሊለው ይገባል ብለዋል።

ወጣቶች ሁሌም ለሰላም ሊቆሙ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክትና ማብራሪያ ከትግራይ ክልል ነባራዊ ሁኔታ ባሻገር የኢትዮጵያን የፖለቲካ አካሄድና ሥርዓት ያሳየ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሚዛን ቴፒ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር ቢመርቅ በርሁን ናቸው።


 

ይህም ለአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ትርጉም እንዳለው ገልጸው፤ በተለይ የትግራይ ወጣቶች በአረጀ አስተሳሰብ ከተቸነከረው የህወሃት ቡድን ራሱን በማላቀቅ ለክልሉ ሰላምና የተሻለ አማራጭ መቆም እንዳለበት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም