ቀጥታ፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገርን የሚጠቅሙ ሀሳቦች ላይ ትኩረት ማድረግ አለባቸው - ምሁራን

አሶሳ፤ የካቲት 29/2018(ኢዜአ)፦ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ስነምግባርን በማክበር በሃሳብ ብቻ መከራከርን በመልመድ ሀገርን የሚጠቅሙ ሀሳቦች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸውየአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን ተናገሩ።

7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማከናወን የዕጩዎች ምዝገባ የተጠናቀቀ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ደግሞ የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ ይገኛል።

በምርጫው ዜጎች የተሻለ ሃሳብ እና ፖሊሲ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ እንዲያስችላቸው የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሃን የምርጫ ቅስቀሳና የሐሳብ ክርክሮችን እያከናወኑ መሆናቸው ይታወቃል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን እንደተናገሩት፤ ምርጫን በህገ መንግስቱ መሠረት በተያዘለት ገደብ ማከናወን አንዱ የዴሞክራሲ መገለጫ ነው።

በዩኒቨርሲቲው የፌዴራሊዝም መምህር ረዳት ፕሮፌሰር አዳሙ ጅባት የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙሃን የሚያደርጉት የምርጫ ቅስቀሳና የሐሳብ ክርክሮች ህብረተሰቡ ስለሚመርጠው ፓርቲ የተሻለ ግንዛቤ እንዲይዝ ያደርጋሉ ብለዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን በነፃነት እያከናወኑት የሚገኘው የምርጫ ቅስቀሳ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የሚያግዝ እና የፓርቲዎች ማኒፌስቶ ለመራጮች ተደራሽ እንዲሆን ያግዛል ነው ያሉት።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫ ቅሰቀሳ ወቅት የሚያነሱት የምረጡኝ ቅስቀሳ ኃላፊነት እና ተጠያቂነት ያለው መሆን እንዳለበትም ገልጸዋል።

የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫ ስነምግባርን በማክበር በሃሳብ ብቻ መከራከርን መልመድ አለባቸው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አዳሙ፤ ሀገርን የሚጠቅሙ ሀሳቦች ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለባቸው ጠቅሰዋል።


 

ሌላው በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር አበበ አኖ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ምርጫ ለአንድ ሀገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮች መፍትሔ ያመጣል ተብሎ ስለሚጠበቅ የዜጎችን ተሳትፎ የሚጠይቅ ነው ብለዋል።

በምርጫ ቅስቀሳ ወቅት የፖለቲካ ፓርቲዎች ዜጎች አሳሳች የሆነ አስተሳሰብ እንዳይዙ በማድረግ ግልፅ ፖሊሲና በምርጫው ቢያሸንፉ ሊፈጽሙት በሚገባው ትክክለኛ ፖሊሲ ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም