246ኛው የሚላን ደርቢ - ኢዜአ አማርኛ
246ኛው የሚላን ደርቢ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2018 (ኢዜአ) ፦ በጣልያን ሴሪአ የ28ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ኤሲ ሚላን እና ኢንተር ሚላን የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
ጨዋታው በሳንሲሮ ስታዲየም ምሽት 4 ሰዓት ከ45 ላይ ይካሄዳል።
ኤሲ ሚላን በውድድር ዓመቱ 27 ጨዋታዎችን አከናውኖ በ16ቱ ድል ሲቀናው ሁለት ጊዜ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ዘጠኝ ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል።
43 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 20 ግቦች ተቆጥረውበታል። ሚላን በ57 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
የከተማ ተቀናቃኙ ኢንተር ሚላን በሊጉ ካደረጋቸው 27 ጨዋታዎች መካከል 22 ጊዜ ሲያሸንፍ አራት ጊዜ ተሸንፏል። በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይቷል።
በጨዋታዎቹ ላይ 64 ግቦችን ሲያስቆጥር 21 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ67 ነጥብ የሊጉ አናት ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ቡድኖች በሁሉም ውድድሮች ሲገናኙ የአሁኑ ለ246ኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው 245 ጨዋታዎች ኢንተር ሚላን 91 ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዟል። ኤሲ ሚላን 83 ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪዎቹ 71 ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
በሴሪአው 183 ጊዜ ተገናኝተው ኢንተር ሚላን 70፣ ኤሲ ሚላን 56 ጊዜ አሸንፈዋል። 57 ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል።
ባለፉት 10 የሴሪአ ግንኙነታቸው ሁለቱም በተመሳሳይ አራት ጊዜ አሸንፈዋል። በቀሪ ሁለት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
በዘንድሮው የውድድር ዓመት በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት ጨዋታ ኤሲ ሚላን በክርስቲያን ፑሊሲች ጎል 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ክለቦቹ ለ117 ዓመታት የዘለቀ ተቀናቃኝነት አላቸው። ኢንተር ሚላን 20 እና ኤሲ ሚላን 19 ጊዜ የሴሪአ ዋንጫን አንስተዋል።
በአህጉራዊ መድረክም ኤሲ ሚላን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን ሰባት ጊዜ በማንሳት ስኬታማው ክለብ ነው። ኢንተር ሚላን ሶስት ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል።
በውድድር ዓመቱ ጠንካራ ፉክክር እያደረጉ የሚገኙት ክለቦች የሴሪአ ጨዋታ የተመልካቾችን ቀልብ ስቧል።
ኢንተር ሚላን ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል። በአንጻሩ ኤሲ ሚላን ድል ከቀናው በዋንጫ ፉክክሩ ወሳኝ ሶስት ነጥብ ያገኛል።
የ48 ዓመቱ ዳንኤሌ ዴቬሪ ተጠባቂውን የደርቢ ጨዋታ በዋና ዳኝነት ይመሩታል።