ቀጥታ፡

የኤፍኤ ካፕ ጥሎ ማለፍ የሶስተኛ ቀን ውሎ

አዲስ አበባ ፤ የካቲት 29/2018 (ኢዜአ)፡- በእንግሊዝ ኤፍኤ ካፕ አምስተኛ ዙር መርሐ-ግብር የሶስተኛ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

 

ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ ፉልሃም ከሳውዝሃምፕተን በክራቨን ኮቴጅ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በአራተኛው ዙር  ፉልሃም ስቶክ ሲቲን፣ ሳውዝሃምፕተን ሌይስተር ሲቲን አሸንፈዋል።

ፉልሃም በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ፣ ሳውዝሃምፕተን በሻምፒዮንሺፕ (ሁለተኛ ዲቪዚዮን) የሚገኙ ክለቦች ናቸው።

 

በሌላኛው መርሐ-ግብር ፖርት ቫሌ ከሰንደርላንድ ከቀኑ 10 ከሰዓት ከ30 ላይ በቫሌ ፓርክ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

በእንግሊዝ ሶስተኛ የሊግ እርከን (ሊግ ዋን) የሚገኘው ፖርት ቫሌ በአራተኛው ዙር ብሪስቶል ሲቲን በማሸነፍ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅሏል።

የፕሪሚየር ሊጉ ክለብ ሰንደርላንድ ኦክስፎርድ ዩናይትድን በመርታት 16 ውስጥ ገብቷል።

 

ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ሊድስ ዩናይትድ ከኖርዊች ሲቲ ይጫወታሉ።

በአራተኛው ዙር ሊድስ ዩናይትድ በርሚንግሃም ሲቲን፣ ኖርዊች ሲቲ ዌስትብሮሚች አልቢዮንን በማሸነፍ ጥሎ ማለፉን ተቀላቅለዋል።

አሸናፊ ቡድኖች ለሩብ ፍጻሜ ያልፋሉ።

ሊቨርፑል፣ አርሰናል፣ ቼልሲ እና ማንችስተር ሲቲ እስከ አሁን ሩብ ፍጻሜውን የተቀላቀሉ ክለቦች ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም