በሴቶች ድምፅና ተሳትፎ የኢትዮጵያ ብልፅግና እውን ይሆናል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶች ድምፅና ተሳትፎ የኢትዮጵያ ብልፅግና እውን ይሆናል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2018(ኢዜአ)፦ በሴቶች ድምፅና ተሳትፎ የኢትዮጵያን ብልፅግና እናረጋግጣለን ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
50ኛው ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ የ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በአዲስ አበባ ተካሄዷል።
ስፖርታዊ መርሃ ግብሩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ነው።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በወቅቱ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሴቶች በሀገር ግንባታና በብልፅግና ጉዞ ውስጥ ያላቸውን የማይተካ ሚና አጽንኦት ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ ስኬተማ ሰዎችና ዝነኛ አትሌት ሴቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፤ ይህ የላቀ ብቃትና ጥንካሬ ትልቅ እውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል።
ሴቶች ለኢትዮጵያ ሰላምና ብልፅግና ትልቅ መስዋዕትነት መክፈላቸውን ያስታወሱት ከንቲባዋ፤ አሁንም ሴቶች ሀገራዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ከወንድሞቻችን ጋር ተሳስረን ሀገራችንን እናሳድጋለን በማለት የሴቶች ተሳትፎ ከወንዶች ጋር በተቀናጀና በተደጋገፈ መልኩ ለሀገር ግንባታ እንደሚውል አመልክተዋል።
ከንቲባዋ መንግሥት የሴቶችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
በብልፅግና ጉዞ ውስጥ የሴቶች የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ተጠቃሚነት በፍትሐዊነት እውን እንዲሆን በትጋት እንደሚሰራም ቃል ገብተዋል።
ሴቶች የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ መሪ ኃይል መሆናቸውን የገለጹት ከንቲባዋ፤ ቀኑን ምክንያት በማድረግ እንኳን አደረሳችሁ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ላለፉት 50 ዓመታት የሴቶች መብትና ድምፅ ትኩረት እንዲያገኝ በተደረገው ጥረት፣ ዛሬ ላይ ለደረሰው ትልቅ ሀገራዊ ለውጥ መሠረት መጣሉን ገልጸዋል።
ሴቶች በፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዘርፎች እያመጡት ያለው ውጤት ለሀገሪቱ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን አውስተዋል።
የሴቶች መብት እንዲከበርና የውሳኔ ሰጪነት ሚናቸው እንዲያድግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመጠቆም፣ እንኳን አደረሳችሁ ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በውድድሩ የተሳተፉ ሴቶች ሩጫው የሴቶችን የአካልና የአዕምሮ ጤና ከመጠበቅ ባለፈ፣ ማህበራዊ ግንኙነትን በማጠናከር ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
በ5 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ከፍተኛ የመንግሥት የስራ ሀላፊዎች ተዋቂ አትሌቶችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።