የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከወላይታ ድቻ ጋር ይጫወታል - ኢዜአ አማርኛ
የሊጉ መሪ ሲዳማ ቡና ከወላይታ ድቻ ጋር ይጫወታል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2018 (ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 23ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር ዛሬ ይጀመራል።
ምሽት 12 ሰዓት ላይ ወላይታ ድቻ ከሲዳማ ቡና በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ወላይታ ድቻ በሊጉ እስከ አሁን ባደረጋቸው 22 ጨዋታዎች በአራቱ አሸንፎ በሰባቱ ተሸንፎ 11 ጊዜ አቻ ወጥቷል። 23 ግቦችን በጨዋታዎቹ ላይ ሲያሳርፍ 25 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ23 ነጥብ 18ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና 22 ጨዋታዎችን አከናውኖ 11 ጊዜ ሲያሸንፍ በሁለቱ ሽንፈት አስተናግዷል። በቀሪ ዘጠኝ ጨዋታዎች አቻ ተለያይቷል። 27 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 11 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ሲዳማ ቡና በ42 ነጥብ ሊጉን እየመራ ነው።
ጨዋታው ወላይታ ድቻ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ፣ ሲዳማ ቡና ተከታታይ ድሉን ለማስመዝገብ ይጫወታሉ።
ሲዳማ ቡና ካሸነፈ የሊጉን መሪነት ያጠናክራል።
በሌላኛው መርሐ-ግብር መቻል ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
መቻል በውድድር ዓመቱ 22 ጨዋታዎችን አድርጎ ዘጠኙን ሲያሸንፍ በስድስቱ ሽንፈት አስተናግዷል። ሰባት ጊዜ አቻ ወጥቷል። 15 ግቦችን በ22ቱ ጨዋታዎች ላይ 29 ግቦችን ሲያስቆጥር 19 ጎሎችን አስተናግዷል። ቡድኑ በ34 ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
በሊጉ ካከናወናቸው 22 ጨዋታዎች መካከል አምስቱን ያሸነፈው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በበኩሉ ስምንት ጊዜ ተሸንፏል። ዘጠኝ ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። 16 ግቦችን ሲያገባ 23 ጎሎች ተቆጥረውበታል።
ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በ24 ነጥብ 17ኛ ደረጃን ይዞ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛል።
መቻል እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በድል ጉዟቸው ለመቀጠል ይፋለማሉ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከኢትዮጵያ ቡና ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።
ኢትዮ ኤሌክትሪክ በ31 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃን ይዟል። ኢትዮጵያ ቡና አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው በ29 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ሁለቱ ቡድኖች በአሸናፊነት መንገድ ለመቀጠል የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ከቀኑ 9 ሰዓት ላይ የሚደረገው ጨዋታ ሸገር ከተማ እና ቅዱስ ጊዮርጊስን ያገናኛል።
ሸገር ከተማ በ24 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዟል። አንድ ተስተካካይ ጨዋታ የሚቀረው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ25 ነጥብ 13ኛ ላይ ተቀምጧል።
ሸገር ከተማ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ድል አልቀናቸውም።
ሁለቱም ቡድኖች ወደ አሸናፊነት መንገድ ለመመለስ ይጫወታሉ።
የ23ኛ ሳምንት መርሐ-ግብር እስከ መጋቢት 1 ቀን 2018 ዓ.ም ይቆያል።
የሲዳማ ቡናው አቤል ያለው፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ አዲስ ግደይ እና የፋሲል ከነማው ታምራት ኢያሱ በተመሳሳይ ስምንት ግቦችን ከመረብ ላይ በማሳረፍ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን በጋራ እየመሩ ነው።