ቼልሲ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል - ኢዜአ አማርኛ
ቼልሲ ሩብ ፍጻሜውን ተቀላቅሏል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 29/2018 (ኢዜአ)፦ በእንግሊዝ ኤፍኤ ካፕ ጥሎ መርሐ-ግብር ቼልሲ ሬክሳምን 4 ለ 2 አሸንፏል።
ትናንት ማምሻውን በሬስኮርስ ግራውንድ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጆሽ አቼምፖንግ፣ አሌሃንድሮ ጋርናቾ፣ ጆአኦ ፔድሮ እና የሬክሳም ግብ ጠባቂ አርቱር ኦኮንኮ በራሱ ላይ ለሰማያዊዎቹ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ሳም ስሚዝ እና ካሉም ዶይል ለሬክሳም ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል።
ጨዋታው በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለት አቻ በመጠናቀቁ ወደ ጭማሪ ሰዓት አምርቷል።
አሌሃንድሮ ጋርናቾ በ96ኛው እና ጆአኦ ፔድሮ በ125ኛው ደቂቃ ያስቆጠሯቸው ጎሎች ቼልሲን ባለድል አድርጓል።
ሉዊስ ብሩንት በ114ኛው ደቂቃ ለሬክሳም ያስቆጠረው ጎል በቪዲዮ የታገዘ ዳኝነት (ቫር) ታይቶ ከጨዋታ ውጪ በመሆኑ ተሽሯል።
የሬክሳሙ ጆርጅ ዶብሰን በመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ማብቂያ ላይ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል። ይህም ቡድኑን ጭማሪ 30 ደቂቃውን በ10 ተጫዋች እንዲጨርስ አስገድዶታል።
ጨዋታው አዝናኝ እንቅስቃሴ ተደርጎበታል።
የስምንት ጊዜ የኤፍኤ ካፕ አሸናፊው ቼልሲ ለሩብ ፍጻሜ አልፏል።
በእንግሊዝ ሁለተኛ ዲቪዚዮን (ሻምፒዮንሺፕ) የሚጫወተው የዌልሱ ሬክሳም የኤፍኤ ካፕ ጉዞው አምስተኛ ዙር ላይ ተገቷል።