ቀጥታ፡

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ለመሳተፍ የምርጫ ካርዳችንን ወስደናል - የምርጫ ካርድ የወሰዱ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2018(ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በመሳተፍ ይጠቅመናል ያልነውን ለመምረጥ የምርጫ ካርዳችንን መውሰዳቸውን በአዲስ አበባ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ካርድ የወሰዱ ነዋሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚያካሄድ አስታውቋል።

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ 47 የፖለቲካ ፓርቲዎች 10 ሺህ 934 ዕጩዎች ማስመዝገባቸውንም መግለጹ ይታወሳል። 

የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ዛሬ ተጀምሯል።

የኢዜአ ሪፖርተሮች በከተማዋ በሚገኙ የምርጫ ጣቢያዎች በመዘዋወር የመራጮች የምዝገባ ሂደት ቅኝት አድርገዋል። 

በአራዳ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ዮሀንስ አሰፋ እንደተናገረው፤ ምርጫ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የእድገትና የልማት ጉዞ የሚያሸጋግር ፓርቲ የምንመርጥበት ኹነት ነው። 


 

ስለሆነም ኢትዮጵያን በልማት ሊያሳድግና ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያደርስ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ ወስጃለሁ ብሏል።

ዕድሜው ለመራጭነት የደረሰ ሁሉ ምርጫ ካርድ በመውሰድ በንቃት መሳተፍ እንዳለበት አመልክቷል።

በጠቅላላ ምርጫ ለሀገር ይበጃል የምለውን ለመምረጥ የምርጫ ካርዱን መውሰዱን የተናገረው ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ ኤልዔዘር ደጉ ነው።


 

ወጣቶች ህገ መንግስታዊ መብታቸውን በመጠቀም መምረጥ እንዲችሉ ምርጫ ካርዳ እንዲወስዱም ጥሪ አቅርቧል።

በጉለሌ ክፍለ ከተማ የመራጭነት ካርድ የወሰዱት አቶ ወርቁ ይርጋው በበከላቸው፤ ኢትዮጵያን ለወደፊት የሚመራና ወደ ተሻለ የዕድገት ደረጃ ሊያሻግር የሚችል ፓርቲ ለመምረጥ የመራጭነት ካርድ መውሰዳቸውን ተናግረዋል፡፡


 

ምርጫ ለሰላምና ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስፈላጊ በመሆኑ የምርጫ ካርድ መውሰዳቸውን የተናገሩት ደግሞ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ነዋሪዋ ወይዘሮ አማረች በሱፍቃድ ናቸው፡፡


 

የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ሰባት ነዋሪ ወጣት እንደሻው ነጋሽ በበኩሉ፤ በመጪው ጊዜ ለዕድገት የሚሰራ ፓርቲ ለመምረጥ የምርጫ ካርድ በመወሰዴ ደስተኛ ነኝ ብለዋል፡፡ 


 

የዘንድሮ ምርጫ በዲጂታል የታገዘ መሆኑ ታአማኒነትን የሚጨምርና የተለያዩ መረጃ መጣረሶችን የሚያስቀር መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም