ቀጥታ፡

የሴቶችን አቅም ለማጎልበትና ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማረጋገጥ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል - ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2018(ኢዜአ)፦ የሴቶችን አቅም ለማጎልበትና ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማረጋገጥ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሴቶችና ማሕበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን(ማርች 8 )  ምክንያት በማድረግ በሴቶች ብቻ ለሚመራው የበረራ ቡድን በስካይላይት ሆቴል ሽኝት ተደርጓል።

አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ115ኛ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ለ50ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን በማስመልከት ከዛሬ ምሽት ጀምሮ በሴቶች የሚመሩ ስምንት በረራዎችን ያደርጋል።


 

በዚሁ መርሃ ግብር የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ(ዶ/ር) የሴቶችን አቅም ለማጎልበትና ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማረጋገጥ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

አየር መንገዱ የኢትዮጵያ ኩራት በመሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የሀገርን ስም ከማስጠራት ባለፈ፣ ሴቶችን በማብቃት ረገድ አርአያነት ያለው ተግባር እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።

አየር መንገዱ የጾታ እኩልነትን፣ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሴቶችን ለማብቃትና እኩል ዕድል ለመፍጠር የግሉ ዘርፍም የበኩሉን ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሴቶች ተቋም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ጃኔት ኪም በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሴቶች ብቻ የተመራ በረራ ማድረጉ ሴቶች ዕድሉ ከተሰጣቸው የማይወጡት እንደሌለ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አየር መንገዱ በአቪዬሽን ዘርፍ እያከናወነ ካለው የላቀ ተግባር በተጨማሪ ሴቶችን በዘርፉ ለማብቃት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም የእኩልነት መርህን በተግባር ለዓለም ያሳየ ተግባር ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ የበረራ መርሃ ግብሩ ከፓይለት እስከ አየር ትራፊክ ተቆጣጣሪነት ያለውን ሂደት ጨምሮ ሙሉ በሙሉ በሴቶች የሚመራ መሆኑን ገልጸዋል።

አየር መንገዱ ላለፉት ተከታታይ ዓመታት በተመረጡ ሀገራት በሴቶች ብቻ የተመራ በረራ ሲያካሂድ መቆየቱን አስታውሰው፤ ዘንድሮም ወደ ጅቡቲ፣ ናይሮቢ፣ ፍራንክፈርትና ድሬዳዋን ጨምሮ ስምንት በረራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።


 

በአሁኑ ወቅት የአየር መንገዱ 40 በመቶ ሰራተኞች እንዲሁም 35 በመቶ አመራሮች ሴቶች ሲሆኑ የሴት ፓይለቶች ቁጥርም 95 ደርሷል ሲሉ ገልጸዋል።

ይህ የበረራ መርሃ ግብር ሴቶች በአቪዬሽን ዘርፉ ያላቸውን ተሳትፎ ይበልጥ ለማጠናከር ትልቅ ፋይዳ እንዳለውም ተመላክቷል።

በሽኝት መርሃ ግብሩ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች እንዲሁም ሴት አብራሪዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም