ቀጥታ፡

''ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ ድል እና የወል ትውስታ'' መጽሐፍ ስሁት የታሪክ አረዳድን ለማረም ትልቅ ፋይዳ አለው

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2018(ኢዜአ)፦ ''ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ ድል እና የወል ትውስታ'' መጽሐፍ ለሕትመት መብቃቱ ስሁት የታሪክ አረዳድን ለማረም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ገለጹ።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተባባሪነት የተዘጋጀው ''ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ ድል እና የወል ትውስታ'' የተሰኘ መጽሐፍ ተመርቋል።


 

በዓድዋ ድል መታሰቢያ በተዘጋጀው የመጽሐፉ ምረቃ መርሃ ግብር ላይ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ታገሰ ጫፎ፣ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል።

በመጽሐፍ ላይ ምርቃት ላይ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፣ ሀጎስ አብርሀ (ዶ/ር)፣ ደቻሳ አበበ (ዶ/ር) እና የመጽሐፉ ደራሲ አሻግሬ ገብረወልድ (ዶ/ር) ምልከታቸውን አጋርተዋል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፤ የዓድዋ ድል ታሪክ ቀያሪ ወታደራዊ ድል ብቻ ሳይሆን ቅኝ ግዛትን የሰበረ የነፃነት ፈር ቀዳጅ የእኩልነት ዓርማ ነው ብለዋል።

''ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ ድል እና የወል ትውስታ'' መጽሐፍ ለሕትመት መብቃቱም ስሁት የታሪክ አረዳድን ለማረም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ገልጸዋል።

በመጽሐፉም ቅድመ አያቶችን በዓድዋ ተራሮች የተቀዳጁትን አንጸባራቂ ድልና በርካታ ጉዳዮችን ቀለል ባለ አቀራረብ ተቀንብቦ ለተደራስያን መቅረቡን ተናግረዋል። 

የዓድዋ ድል ለሀገረ መንግስትና የወል ትርክት ግንባታ ወሳኝ ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በመጽሐፉም የታሪክ ጉድለቶችን በመሙላት የዓድዋ ድልን ምሉዕነት በሚያሳይ መልኩ ተተርኮ ቀርቧል ብለዋል።

ሌላኛው በመጽሐፉ ላይ ዳሰሳ ያቀረቡት የታሪክ ምሁር ሀጎስ አብርሀ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በመጽሐፉ የዓድዋ ድልን ከማወዳደር ይልቅ የጋራ ታሪክና የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መሆኑን በተግባር አትቷ ብለዋል።


 

በመጽሐፉ ላይ ተቀንብበው የቀረቡ ሃሳቦችም ለቀጣይ ጥናትና ምርምር እንዲሁም አሰባሳቢ ትርክት ግንባታን ለማጎልበት በማጣቀሻነት የሚያገለግል መሆኑን ገልጸዋል።

የታሪክ ምሁር ደቻሳ አበበ (ዶ/ር)፤ በመጽሐፉ ላይ የተከተቡ ወሳኝ ጽንሰ ሃሳቦች የዓድዋ ድልን በአግባቡ በመተረክ የትውልዱን የታሪክ አረዳድ የሚቀርጽ ነው ብለዋል።


 

ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ ድል እና የወል ትውስታ መጽሐፍ ደራሲ አሻግሬ ገብረወልድ (ዶ/ር)፤ የመጽሐፉ መታሰቢያነት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊ አንድነት መስዋዕትነት ለከፈሉ ሆናል ብለዋል።

በጽሐፉም የተለያዩ ሰነዶችን በማጣቀስ የዓድዋን የድል ታሪክ በቅጡ የከተበና ለአዳዲስ የታሪክ ትናትና ምርምር ሥራዎች መነሳሳትን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

''ዓድዋ የኢትዮጵያውያን ዘመን ተሻጋሪ ድል እና የወል ትውስታ'' መጽሐፍ ለስኬት እንዲበቃ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም