በክልሉ በቆላማ አካባቢዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በቆላማ አካባቢዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል
ጂንካ፤ የካቲት 28/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢዎች ልማት ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው የ2018 ዓ/ም ግማሽ ዓመት የስራ አፈፃፀሙን በጂንካ ከተማ እየገመገመ ነው።
የቢሮው ኃላፊ ኤካል ነትር በወቅቱ እንደገለፁት፤ ቢሮው በቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ የማህበረሰብ ክፍሎችን በዘላቂነት መለወጥ የሚያስችሉ የተቀናጁ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ነው፡፡
በተለይም ለድርቅ ተጋላጭ በሆኑ ቆላማ አካባቢዎች የሚኖሩ የማህበረሰብ ክፍሎች ከዝናብ ጥገኝነት ተላቀው የመስኖ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችሉ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል፡፡
የአየር ንብረት ተፅእኖውን በመቋቋም የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከሚተገበሩ ፕሮጀክቶች መካከል የመስኖ ልማት አንዱ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም በቆላማ አካባቢዎች ሰፋፊ የመስኖ አውታሮችን በመገንባት አርብቶ አደሩ በግብርና ልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆን መደረጉን ገልጸዋል።
በመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራትም የአንድ ከፍተኛ እና የሁለት መካከለኛ ግድቦች የግንባታ ስራ መጀመሩን ጠቁመው፥ ወደ 8 የሚሆኑ አነስተኛ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ደግሞ በተያዘው ዓመት መጨረሻ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በተያዘው ዓመት ከሚጠናቀቁ ፕሮጀክቶች መካከል የአርጎባ፣ ብላቴኤታ፣ ማርቃላሾ፣ ሎማቴ እና ሳላ የተሰኙ እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
ከጊዜ ወደ ጊዜ በአካባቢው በመስኖ የማልማት ፍላጎት እያደገ በመምጣቱ አርብቶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩን ያማከለ የመስኖ ፕሮጀክቶችን ማስፋፋት የሚያስችል የጥናትና ዲዛይን ስራ እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል።
ከመስኖ ልማት ባሻገር በግጦሽ ሳር ከለላ፣ በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ፣ በንፁህ መጠጥ ውሃና በመንገድ መሰረተ ልማት ዝርጋታ፣ በእንስሳት ግብይት ማዕከላት ግንባታና በሌሎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ተናግረዋል፡፡
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ልዩ አማካሪ ቦሼ ቦምቤ(ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ቢሮው በአርብቶ አደሩ አካባቢ ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የጀመረው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን ገልፀዋል።
አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሩን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ በዘላቂነት ኑሮውን ለማሻሻል የተጀመረው የመስኖ ልማት እንዲጠናከር የክልሉ መንግስት በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡
በተለይ በግንባታ ላይ ያሉ የመስኖ ፕሮጀክቶች በአጭር ጊዜ ተጠናቅቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ የተቀናጀ ርብርብ እንደሚደረግም ተናግረዋል።
የአሪ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብረሃም አታ በበኩላቸው፤ በዞኑ ቆላማ አካባቢዎች የተጀመሩ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች የከፊል አርሶ አደሩን ምርታማነት በማሻሻል በግብርና ልማት ተጠቃሚነቱ እንዲያድግ አድርጓል ብለዋል።
የመስኖ ልማት መተግበር ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዓመቱን ሙሉ ለማልማት አቅም በመፈጠሩ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ እንዳስቻለም ተናግረዋል፡፡