የአባያና ጫሞ ሀይቆችን ከስጋት መታደግ የሚያስችል የተቀናጀና በጥናት የተደገፈ ስራ ይሰራል - ኢዜአ አማርኛ
የአባያና ጫሞ ሀይቆችን ከስጋት መታደግ የሚያስችል የተቀናጀና በጥናት የተደገፈ ስራ ይሰራል
አርባ ምንጭ፤ የካቲት 28/2018 (ኢዜአ)፦ የስምጥ ሸለቆ ተፋሰስ የሆኑ የአባያና ጫሞ ሀይቆችን ከስጋት ለመታደግ የተቀናጀና በጥናት የተደገፈ ስራ እንደሚሰራ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ገለጹ።
በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ አስተባባሪነት የአባያና ጫሞ ሀይቆች የሚያስከትሉትን ተጽእኖ መቀነስ የሚያስችል የባለድርሻ አካላት ውይይት በአርባ ምንጭ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በዚህ ጊዜ እንደገለጹት የአባያና ጫሞ ሀይቆችን በአግባቡ መጠቀም ባለመቻሉ ከፀጋነት ወደ ስጋትነት እየተቀየሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በተለይ በጋሞ፣ በጋርዱላ፣ በኮንሶና በቡርጂ ዞኖች የሚገኙ አርሶ አደሮችን ማሳ እንዲሁም በተለያዩ መሠረተ ልማቶች ላይ አደጋ እያስከተሉ ይገኛሉ ብለዋል።
በመሆኑም ሐይቆቹን ከስጋት ለመታደግ የተቀናጀና በጥናት የተደገፈ ስራ እንደሚጠናከር ገልጸዋል፡፡
ተፋሰሶቹ የተፈጥሮ ስነ-ምህዳር፣ የፍራፍሬ፣ የብዝሃ ህይወት የቱሪዝምና የቀጣናዊ ልማት ማሳለጫዎች መሆናቸውን ጠቅሰው ከስጋት ወደ ሀብት ምንጭነት ለመቀየር የባለድርሻ አካላት ሚና ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
በውሃው ዘርፍ የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የዘርፉን ችግሮች ለመቅረፍ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው የክልሉ መንግስት የበኩሉን እንደሚወጣም አረጋግጠዋል።
የማዕድን ሚኒስትርና የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በበኩላቸው የአባያና ጫሞ ሃይቆችን በዘላቂነት መጠቀም ለሃገር ሁለንተናዊ ብልጽግና ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡
በአርባ ምንጭና አካባቢው መልከ ብዙ ፀጋዎች መኖራቸውን ጠቅሰው የሀይቆቹን ትሩፋት ለማጉላት የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ በአግባቡ ሊከናወን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
በተገኙ ጥናቶች መሠረት የተፋሰሶቹን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የተለያዩ ፕሮግራሞች፣ ስትራቴጂዎችና ፕሮጀክቶች ተቀርጸው መተግበር እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
የአባያና ጫሞ ሀይቆች የውሃ መጠን መጨመር፣ የተፋሰሱ ወንዞች ሙላትና ደለል ከፍተኛ አካባቢያዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽዕኖዎችን እያስከተሉ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አብደላ ከማል(ዶ/ር) ናቸው።
የአባያና ጫሞ እንዲሁም ሌሎች ተፋሰሶች በተቀናጀ ሁኔታ ካልተመሩ ተጽዕኖው ከሀይቆቹ ዳርቻ አልፎ ሰፊ ቦታዎችን ሊያዳርስ እንደሚችል በጥናት መረጋገጡንም ጠቅሰዋል።
ዩኒቨርሲቲው በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ምክንያቶች የሚከሰቱ ተግዳሮቶችን በሳይንሳዊ መንገድ ለመከላከል የጀመረውን ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ተናግረዋል።
በመድረኩ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ የስራ ኃላፊዎችና ተመራማሪዎች፣ ባለሀብቶች፣ የጋሞ ሀገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶችና ሌሎችም እየተሳተፉ ነው።