ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤን ታስተናግዳለች

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ(ASMIS) ልታስተናግድ ነው።

ጉባኤውን የሚያዘጋጁት ፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ (POA) እና ኤ.ጂ.ኤ ቴክ (AGA-Tech) ኢንተርፕራይዝ የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ጉባኤው እ.አ.አ ግንቦት 7 እና 8 ቀን 2026 በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።

የመጀመሪያ የሆነው ይህ ጉባኤ የአፍሪካ ተፅዕኖ ፈጣሪ ድምፆችን ከመገናኛ ብዙኅን ድርጅቶች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና የግሉ ዘርፍ መሪዎች ጋር የሚያገናኝ ታሪካዊ የጋራ መድረክ መሆኑ ተገልጿል።

''ተፅዕኖ ለተሻለች አፍሪካ'' በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው ጉባኤው የዲጂታል ተሳትፎ ፈጠራ፣ ቴክኖሎጂና ኃላፊነት ላይ ምክክር የሚደረግበት ወሳኝ መድረክ እንደሚሆንም ይጠበቃል።


 

የፐልስ ኦፍ አፍሪካ ሚዲያ አስተባባሪ በረከት ሲሳይ እንደገለጹት፤ ጉባኤው ፈጣን ዕድገት እያስመዘገበ ባለው ሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ የአፍሪካን የዲጂታል ገጽታና ይዘት ፈጠራ ላይ ትኩረት ያደርጋል ብለዋል።

በጉባኤ የቴክኖሎጂ ሥነ-ምኅዳር ፈጠራ፣ የአፍሪካ ታሪክና መፃኢ ተስፋዎች ላይ ጥራት ያላቸው የይዘት ሥራዎችን ለማስተጋባት አቅም የሚፈጠር አህጉራዊ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

ሁነቱ በአፍሪካ ሀገራትና በዓለም ዙሪያ የሚሰሩ ከ200 በላይ ተፅዕኖ ፈጣሪ የማህበራዊ ሚዲያ ግለሰቦች ተሰባስበው የሚመክሩበት መሆኑንም ተናግረዋል።

የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦቹ በዘላቂ ልማት፣ ዲጂታል አስተዳደርና የይዘት ፈጠራ አቅምን የሚያጎለብቱ የምክክርና የትውውቅ መርሃ ግብሮች እንደሚያካሄዱ አብራርተዋል።

በሰው ሰራሽ አስተውሎት ልምድና ተሞክሮ የሚለዋወጡበት፣ የአፍሪካን ዕድገት በዲጂታል ሥርዓት መግለጥ የሚያስችል እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጠሪዎችን ከትላልቅ የንግድ ድርጅቶች ጋር የሚያገናኝ መድረክ መሆኑንም አንስተዋል።


 

የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ፕሮጀክት አስተባባሪ ባዩሽ ማሞ በበኩላቸው፤፤ ጉባኤው እያደገ በመጣው የዲጂታል ዓለም የአፍሪካን የዲጂታል ሥነ-ምኅዳር ትብብርና ተወዳዳሪነት ለማጎልበት አቅም ይፈጥራል ብለዋል።

በአዲስ አበባ የዓድዋ ድል መታሰቢያ የሚካሄደው የአፍሪካ የማህበራዊ ሚዲያ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ጉባኤ ይፋዊ ምዝገባ በቅርቡ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

በዚህም የይዘት ፈጣሪዎች፣ ተፅዕኖ ፈጣሪዎችና ባለድርሻ አካላት ጉባኤውን የሚመለከቱ ወቅታዊ መረጃዎችን ለማግኘት በ www.asmis.org ድረ-ገጽን መከታተል እንደሚችሉ ገልጸዋል።

የአህጉሪቱን ዲጂታል መጻኢ የፈጠራ አቅምና እጣ ፈንታ በተሻለ ይዘት ለመቅረጽ ጉባአው ወሳኝ መሆኑን ተናግረው ታላላቅ የንግድ ተቋማትና ድርጅቶችም ለጉባኤው ስኬታማነት በአጋርነት እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም