በኦሮሚያ ክልል የመንገድ ተደራሽነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተፋጠኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የመንገድ ተደራሽነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት እየተፋጠኑ ነው
አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል የመንገድ ተደራሽነትን ማረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራት መጠናከራቸውን የክልሉ መንገድና ሎጂስቲክስ ቢሮ ገለጸ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ ኢንጂነር መሐመድ ኑራ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ የመንገድ ተደራሽነትን ለማስፋትና የመንገድ አስተዳደርን ለማዘመን ከባለድርሻ አካላት ጋር የተለያዩ ተግባራት በቅንጅት እየተሠሩ ነው።
በበጀት ዓመቱ በክልል ደረጃ የሚገነቡ በርካታ መንገዶች መኖራቸውንና ከእነዚህ መካከልም ያደሩ 21 መንገዶችና አዳዲስ ደግሞ 4፣ በአጠቃላይ 25 የመንገድ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ በመንግሥት በጀት፣ ኅብረተሰቡን በማሳተፍና በሌሎች የገቢ ምንጮች የመንገድ ግንባታና ጥገና እንዲሁም የድልድዮችና የፓርኪንግ ፕሮጀክቶች ግንባታ በስፋት መከናወኑን ገልጸዋል።
በገጠር የመንገድ ልማት መርሃ ግብር በዞኖችና ወረዳዎች 503 ኪሎ ሜትር ለመገንባት ታቅዶ እስካሁን 75 ኪሎ ሜትር ግንባታው መጠናቀቁን አንስተዋል።
በተጨማሪም በዚህ ዓመት 21 ትላልቅ ድልድዮች በክልል ደረጃ ለመገንባት ታቅዶ አፈጻጸማቸው 56 በመቶ መድረሱንም ተናግረዋል።
ከመንገድ ግንባታ ሥራው ጎን ለጎን በአሰላ፣ ፊቼ፣ ጊምቢ፣ ነቀምቴና ቡሌ ሆራ ከተሞች ዘመናዊ መነኸሪያ ግንባታ እየተፋጠነ ነው ብለዋል።
የመንገድ አስተዳደርን በማዘመን የአገልግሎት ጊዜውን ለማራዘም የመንገዶቹ ጥገናና እንክብካቤ ላይ ትኩረት መደረጉንም አክለዋል።