የወጣቶችን ስብዕና በሚያንጹ ተግባራት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይገባል - ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የወጣቶችን ስብዕና በሚያንጹ ተግባራት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይገባል - ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2018 (ኢዜአ)፡- የነገዋን ሀገር የሚመሩ ወጣቶችን ስብዕና ማነፅ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ኢንቨስት ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) አስገነዘቡ።
በዘመናዊ መልክ ዕድሳት የተደረገለት፣ ልዩ ልዩ ቁሳቁስ የተሟላለት እና አዲስ የተገነባ የስፖርት መጫወቻ ሜዳን ያካተተው የአጋሮ ከተማ የወጣቶች ስብዕና ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
ሚኒስትሯ የማዕከሉ አገልግሎት ማስጀመሪያ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ለዘላቂ ሰላም እና ለሀገራችን ብልጽግና የዛሬውም ሆነ የወደፊት ሀገር መሪ ወጣቶችን ስብዕና ማነፅ በሚያስችሉ ተግባራት ላይ ኢንቨስት ማድረግ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ብለዋል።
ማዕከሉ የመንግሥት፣ የማኅበረሰቡና የአጋር አካላት የተቀናጀ ጥረት ብሎም የመደመር ውጤት ነው ማለታቸውን ሚኒስቴሩ ለኢዜአ የላከው መረጃ አመላክቷል።
በከተማውና አካባቢው የሚገኙ ወጣቶች በማዕከሉ በአግባቡ እንዲገለገሉና አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያደርጉም አሳስበዋል።
ወጣቶች በመልካም ስብዕና ታንፀው፣ ዕውቀታቸው ዳብሮ፣ እጃቸው በክኅሎትና በሙያ ተፍታትቶ ከአካባቢያቸው ባለፈ ለሀገር ብልፅግና ጉልህ አስተዋፅዖ እንዲያበረክቱም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ማዕከሉ የዲጂታል ቤተ-መጻሕፍት፣ የአይ ሲ ቲ፣ የሥልጠና አዳራሾች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች፣ ካፍቴሪያና የምክር አገልግሎትን መስጠት በሚያስችል መልኩ ከማዘመንና ከእድሳት በተጨማሪ በልዩ ልዩ ቁሳቁስ እንዲሟላ መደረጉንም አረጋግጠዋል።
ሚኒስቴሩ በሌሎችም አካባቢዎች የሚገኙ ማዕከላትን ከማዘውተሪያነት ባለፈ ወደ ስብዕና ማበልፀጊያነት እንዲሸጋገሩ ብሎም የተሟላ፣ ዘመናዊና ሁለገብ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል በቅንጅት ይሠራል ብለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት የሥነ-ሕዝብ ፈንድ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኮፊ ኩዋሜ በበኩላቸው፤ እያንዳንዱ ወጣት እምቅ ዐቅሙን የሚጠቀምበት ዓለም እውን ለማድረግ አስፈላጊውን የቴክኒክ፣ የማቴሪያልና የዐቅም ግንባታ ድጋፍ እናደርጋለን ነው ያሉት።