ቀጥታ፡

አዲስ አበባ የአፍሪካ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ፎረምን ታስተናግዳለች

አዲስ አበባ፤ የካቲት 28/2018 (ኢዜአ)፦ ስምንተኛው የአፍሪካ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ፎረም ሚያዚያ 18 እና 19 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (ኢሲኤ) ያዘጋጀው ፎረም “ አጀንዳ 2030 እና አጀንዳ 2063ን በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ዲጂታል ኢኖሼሽን ውጤታማ ማድረግ” በሚል መሪ ሀሳብ ይካሄዳል።

ፎረሙ የአፍሪካ ፖሊሲ አውጪዎች፣ ተመራማሪዎች፣ ኢኖቬተሮች እና የልማት አጋሮች በአንድ መድረክ ያገናኛል።

ባለድርሻ አካላቱ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ በአፍሪካ ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ ያለውን ሚና አስመልክቶ በፎረሙ ይመክራሉ።

መድረኩ የአፍሪካ የኢኖቬሽን አጀንዳን የበለጠ ለማራመድ የሚያስችል ቁልፍ ማዕቀፍ ሆኖ እንደሚያገለግልም ኢዜአ ከኢሲኤ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

በመንግስት፣ በአካዳሚክ ማህበረሰቡ፣ በኢንዱስትሪ እና ዓለም አቀፍ ተቋማት መካከል ያለውን ትብብር ማጠናከር በሚቻልበት ሁኔታ ላይም ውይይት ይደረጋል።

ፎረሙ አፍሪካ በዘላቂ ልማት ግቦች የደረሰችበትን የአፈጻጸም ደረጃ ይገመግማል።

ውሃ እና ንጽህና፣ ተመጣጣኝ እና ንጹህ ኢነርጂ፣ ኢንዱስትሪ እና መሰረተ ልማት፣ ዘላቂ ከተሞችና የልማት አጋርነት ጨምሮ የተለያዩ የዘላቂ ልማት ግቦችን የተመለከተ ውይይት ይካሄዳል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች ኢኖቬሽን ተኮር መፍትሄዎች እና ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር የሚያስችሉ የተግባር እርምጃዎች ላይ ምክረ ሀሳባቸውን ያቀርባሉ።

በፎረሙ ላይ ሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ ከፍተኛ አዎንታዊ ለውጥ ያመጡ ቴክኖሎጂዎች፣ ጀማሪ የስራ ፈጠራዎች (Startups)፣ የምርምር ኢኒሼቲቮች እና የኢኖቬሽን ማዕከላት ስራዎች ለእይታ ይቀርባሉ።

ኹነቱ የእውቀት ሽግግርን ለማሳለጥ፣ በዩኒቨርሲቲዎች እና ምርምር ተቋማት መካከል ያለውን አጋርነት ማጠናከር እንዲሁም በአፍሪካ ያለውን የቴክኖሎጂ ሽግግር የመደገፍ አላማ አለው።

በፎረሙ ላይ የአፍሪካ ሀገራት መንግስታት ተወካዮች፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን እና የአፍሪካ ልማት ባንክ አመራሮች፣ የግሉ ዘርፍ ተዋንያን፣ የትምህርት ተቋማት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአፍሪካ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ፎረም ውጤቶች በአዲስ አበባ የሚካሄደውን 12ኛው የአፍሪካ ቀጣናዊ የዘላቂ ልማት ፎረም የሚደግፉ መሆናቸው ተመላክቷል።

12ኛው የአፍሪካ ቀጣናዊ የዘላቂ ልማት ፎረም ከሚያዚያ 20 እስከ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም