ቀጥታ፡

የኤፍኤ ካፕ ባለ ብዙ ክብሩ አርሰናል ከማንስፊልድ ታውን ጋር ይጫወታል

አዲስ አበባ ፤ የካቲት 28/2018 (ኢዜአ)፡- በእንግሊዝ ኤፍኤ ካፕ አምስተኛ ዙር መርሐ-ግብር የሁለተኛ ቀን ውሎ ሶስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።

ከቀኑ 9 ሰዓት ከ15 ላይ በፊልድ ሚል ስታዲየም ማንስፊልድ ታውን ከአርሰናል ይጫወታሉ።

በአራተኛው ዙር ማንስፊልድ በርንሌይን፣ አርሰናል ዊጋን አትሌቲክን አሸንፈዋል።

ሁለቱ ክለቦች በኤፍኤ ካፑ ሲገናኙ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።

ከዚህ ቀደም እ.አ.አ በ1929 በአራተኛ ዙር ተገናኝተው አርሰናል 2 ለ 0 አሸንፏል።

ከ97 ዓመታት በኋላ በድጋሚ በኤፍኤ ካፕ ውድድር ይገናኛሉ።

ማንስፊልድ ታውን በውድድሩ ትልቁ ውጤቱ እ.አ.አ 1968/59 ሩብ ፍጻሜ የገባበት ነው። አርሰናል 14 ጊዜ የኤፍኤ ካፕ ዋንጫን በማንሳት ስኬታማው ክለብ ነው።

መድፈኞቹ ለመጨረሻ ጊዜ ውድድሩን ያሸነፉት እ.አ.አ በ2020 ነበር።

ማንስፊልድ ታውን በእንግሊዝ እግር ኳስ ሊግ ሶስተኛ እርከን (ሊግ ዋን) የሚጫወት ቡድን ነው።

አርሰናል የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን በ64 ነጥብ እየመራ ነው።

ጨዋታውን አርሰናል የማሸነፍ ከፍተኛ ግምት ወስዷል።

 

በሌሎች መርሐ-ግብሮች ሬክስሃም ከቼልሲ ምሽት 2 ሰዓት ከ45፣ ኒውካስትል ዩናይትድ ከማንችስተር ሲቲ ምሽት አምስት ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።



ትናንት ማምሻውን በተደረገ የኤፍኤ ካፕ የመጀመሪያ የጥሎ ማለፍ ጨዋታ ሊቨርፑል ዎልቭስን 3 ለ 1 በማሸነፍ ለሩብ ፍጻሜ አልፏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም