በሴቶች ላይ የሚደርስ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ ጥቃት ለመከላከል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በንቃት ሊሰሩ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
በሴቶች ላይ የሚደርስ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ ጥቃት ለመከላከል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በንቃት ሊሰሩ ይገባል
አዲስ አበባ፤ የካቲት 27 /2018(ኢዜአ)፦ በሴቶች ላይ የሚደርስ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ ጥቃትን ለመከላከል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የህብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግ ረገድ በንቃት መስራት እንዳለባቸው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን አስገነዘበ።
5ኛው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት "ራስን መቻል ለዘላቂ ሰላምና አካታች ልማት" በሚል መሪ ሀሳብ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬሽን ማዕከል መከፈቱ ይታወቃል።
የዚሁ መርሃ ግብር አካል የሆነ የ'ኢምፓዚ ፎር ላይፍ ኢንተግሬትድ ዲቨሎፕመንት አሶሴሽን' (ኤሊዳ) (ELIDA) የተዘጋጀ በሴቶች ላይ የሚደርስ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ ጥቃት መከላከል ላይ ያተኮረ የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ሳምንት ሶስት አላማዎችን ያነገበ ነው።
እነዚህም ትብብር እና ቅንጅትን ማጠናከር፣ መልካም ተሞክሮዎችን መጋራት እና ለፖሊሲ የሚሆኑ ግብዓቶችን ማሰባሰብ መሆኑን ተናግረዋል።
በሴቶች ላይ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ ጥቃት መከላከል ላይ ያደረገው ውይይትም ከዓላማዎቹ አንጻር ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሀገር ግንባታና በዜጎች ተጠቃሚነት ላይ ትኩረት አድርገው፣ ችግሮች ከመከሰታቸው በፊት በንቃትና መስራት እንዳለባቸውም ገልጸዋል።
ጠንካራ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ዕድሎችንና ፈተናዎችን ቀድሞ በመለየት ዘመኑን የዋጀ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።
በተለይም በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መምጣታቸውን አንስተዋል።
የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ቴክኖሎጂን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከል የኅብረተሰቡን ግንዛቤ በማሳደግና ጉዳዩን የጋራ አጀንዳ በማድረግ በንቃት መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ደርጅቶች ምክር ቤት ዋና ዳይሬክተር ተረፈ ዴጌቲ በበኩላቸው፣በሴቶች ላይ የሚደርስ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ ጥቃትን በህግ እና በፖሊሲ ማእቀፎች መከላከል እንደሚገባ ገልጸዋል።
ለዚህም የሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፎም ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።
የ'ኢምፓዚ ፎር ላይፍ ኢንተግሬትድ ዲቨሎፕመንት አሶሴሽን' (ኤሊዳ) ዋና ዳይሬክተር ዚነት ይመር ማህበሩ ላለፉት 18 ዓመታት በሴቶች ትምህርት፣ በሰላም ግንባታ እና በኢኮኖሚ ማብቃት ላይ ሰፊ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።
ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በሴቶች ላይ የሚደርሰው ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ ጥቃት እየጨመረ መምጣቱ የሴቶችን ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ እየገደበው መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህንን ችግር ለመከላከልም የሁሉንም አካላት ትብብር፣ ቅንጅት እና አሳታፊ ምህዳር መፍጠር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ማህበሩም ይህንን የጥቃት አይነት በዘላቂነት ለመፍታት በተለያዩ አካባቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን በስፋት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የፕሮጀክት አመራር፣ ትብብር እና የሀብት ማሰባሰብ ቡድን መሪ ሳምሶን ኒሻን ችግሩን ለመከላከል የሴቶች የፖሊሲ ክለሳ ተደርጎ በመጨረሻ ረቂቅ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ይህም ጉዳቱን ለመከላከል ጠንካራ መሰረት እንደሚጥል ገልጸው በስትራቴጂዎችም የተቀመጡ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።
ከዲጂታል እውቀት አንጻር ውስንነቶች መኖራቸውን አንስተው ተጠቂዎችም ሰፊ የግንዛቤ ክፍተት እንዳለባቸው ገልጸዋል።
የሴት መብት ተሟጋች እና በሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እንዲሁም በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ የምትሰራው ሰላማዊት ተዘራ ህጎች ቢኖሩም ሰፊ የአፈጻጸም ክፍተት መኖሩን አንስታለች።
በቴክኖሎጂ እውቀት ረገድ ሰፊ ክፍተት መኖሩን ገልፀው፣ ችግሩን ለመቅረፍ ተከታታይነት ያላቸው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች መሰጠት እንዳለባቸውም ተናግራለች።
በሴቶች ላይ የሚደርስ ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ ጥቃት ከፍተኛ የስነ ልቦና ጫናን የሚፈጥር መሆኑን የገለጸችው ደግሞ የሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እና የማህበራዊ አካታችነት ጥናት ባለሙያ ሀና ለማ ናት።
ድርጊቱ ዝቅ ተደርጎ ሳይታይ ተገቢው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልፃለች።