ቀጥታ፡

በከተማው ዳሞታ ተራራን ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችሉ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ ነው

ወላይታ ሶዶ፤ የካቲት 27/2018 (ኢዜአ)፡-በወላይታ ሶዶ ከተማ የዳሞታ ተራራን ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችሉ የልማት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የከተማው ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ፡፡

የከተማው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት መምሪያ በበኩሉ ግንባታውን በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ ገልጿል።

መንግስት ለቱሪዝም ዘርፍ ትኩረት በመስጠት በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ቱሪዝምን ለማሳደግ ግብ ጥሎ እየሰራ መሆኑ የሚታወቅ ነው።

የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደርም ከ20 በላይ ነባርና አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የማልማትና ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ተግባራትን እያከናወነ ነው፡፡

የከተማው ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሪት ወይንሸት መና ለኢዜአ እንደገለጹት ዳሞታ ተራራን ምቹ የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ የሚያስችሉ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡

በዳሞታ ተራራ ላይ የተጀመረው የ7ሺህ 187 የደረጃ መወጣጫ ኢኮ ቱሪዝም ሳይት ግንባታ በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ግንባታው በከተሞች አንድ የቱሪዝም መዳረሻ የማልማት ውጥን አካል መሆኑን የገለጹት ሃላፊዋ ሲጠናቀቅም የከተማዋን የቱሪስት ፍሰት በመጨመር ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ያሳድጋል ብለዋል።


 

የከተማው ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት መምሪያ የከተማ የተቀናጀ መሠረተ ልማት ሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አስራት ዳዊት በበኩላቸው፣ የዳሞታ ኢኮ ቱሪዝም ሳይት የደረጃ መወጣጫ ግንባታ በሦስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ እየተገነባ ነው ብለዋል፡፡

የመጀመሪያውን ዙር ግንባታ በ90 ቀናት ለማጠናቀቅ ከተቋራጩ ጋር ውል በመግባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመወጣጫ ደረጃው በጠቅላላው 5 ነጥብ 3 ኪሎ ሜት ርዝመት ያለው ሲሆን ለቱሪስቶች አገልግሎት የሚሰጡ ሌሎች መዝናኛ ቦታዎችና ተጨማሪ የመንገድ ግንባታን ያካተተ መሆኑም አመልክተዋል።

ለመጀመሪያ ዙር ግንባታ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉን የጠቆሙት አስተባባሪው፣ ለልማቱ በአጠቃላይ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት መያዙን ጠቅሰዋል።

ግንባታው ሲጠናቀቅ ለቱሪስት ፍሰትና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ካለው ጥቅም አንፃር በልዩ ትኩረት እየተመራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የሳይቱ ግንባታ በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ምሽት ጭምር እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ ግንባታውን የሚያከናውነው ሥራ ተቋራጭ አንጆኒዮ ኮንስትራክሽን ሳይት መሀንዲስ መኮንን ተስፋዬ ናቸው፡፡


 

በግንባታ ሳይቱ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው አቶ ተገኝ ፉርቻካ እና አቶ ኦሎሞ አሰፋ የግንባታው መጀመር የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚ እንዳደረጋቸው ገልጸዋል፡፡


 

የቱሪዝም መዳረሻው ሲጠናቀቅ ለአካባቢው ተጨማሪ ዕድልና ተስፋ ይዞ እንደሚመጣ በማመን ሥራቸውን በአግባቡ እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም