ለመራጭነት የሚያስችላቸውን ካርድ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን የባህርዳርና የጀረር ዞን ነዋሪዎች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ለመራጭነት የሚያስችላቸውን ካርድ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን የባህርዳርና የጀረር ዞን ነዋሪዎች ገለጹ
ባህር ዳር/ጀረር፤ የካቲት 27/2018 (ኢዜአ)፡-በዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ የሚፈልጉትን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን የባህር ዳር ከተማ እና በሶማሌ ክልል የጀረር ዞን ነዋሪዎች ገለፁ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሔደው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ፣ ሰላማዊ፣ ተአማኒና አሳታፊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የጊዜ ሰሌዳ አውጥቶ እየሰራ ይገኛል።
መራጮች መዝገባም ነገ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚጀመር ቦርዱ ያሳወቀ ሲሆን ኢዜአም በባህርዳር ከተማና እና በሶማሌ ክልል ጀረር ዞን ከተሞች ነዋሪዎች መምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ ለመውሰድ ያላቸውን ዝግጁነት በማስመልከት አነጋግሯል።
በባህር ዳር ከተማ ኢዜአ ካነጋገራቸው ነዋሪዎቹ መካከል አቶ ሰይፈአርዕድ ሙሏለም እንደገለጹት ዘንድሮ በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ይመራኛል፤ ያስተዳድረኛል ብለው ያመኑበትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ከወዲሁ እየተዘጋጁ ነው።
እንደሀገር ቀደም ሲል በተካሄዱ ምርጫዎች በንቃት በመሳተፍ በዴሞክራሲያዊ መንገድ መብታቸውን ማረጋገጣቸውን አስታውሰዋል።
ነገ በሚጀምረው የመራጮች ምዝግባም የምርጫ ካርድ በመውሰድ በምርጫው እለት ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በአግባቡ ለመጠቀም መዘጋጀታቸውን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማረጋገጥ፣ ሀገረ መንግስቱን ለማጽናትና ልማትን ለማፋጠን ዴሞክራሲያዊ ምርጫ አስፈላጊና ወሳኝ መሆኑን የተናገሩት ነዋሪዋ፣ ህብረተሰቡ በምርጫው ለመሳተፍ በወቅቱ በመመዝገብ የመራጭነት ካርድ መውሰድ እንዳለበት ገልጸዋል።
ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ማረጋገጥና የፈለግነውን ፓርቲ መምረጥ የምንችለው የምርጫ ካርድ በወቅቱ ስንይዝ ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ አማረ ጌጡ ናቸው።
በተመሳሳይ በሶማሌ ክልል የጀረር ዞን ነዋሪዎችም በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ይበጀናል ያሉትን ፓርቲ ለመምረጥ የሚያስችላቸውን ካርድ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ የዞኑ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ሃይብ ሳላህ በምርጫው ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ ለመውሰድ ቀኑን እየተጠባበቁ ናቸው።
በተለይ የሴቶችን እኩል ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚሰራ የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ መዘጋጀታቸውንም ተናግረዋል።
"በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ይሆነኛል የምለውን ፓርቲ ለመምረጥ ተዘጋጅቺያለሁ" ያሉት ደግሞ አቶ አብዱላሂ ዊል መሀሙድ ናቸው።
በተለይ ለአገር አድገት ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥና ተግቶ የሚሰራ የፖለቲካ ፓርቲ ምርጫቸው መሆኑን ገልጸው፣ ይህን ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን በአግባቡ ለመጠቀም በነገው እለት የመራጮች ምዝገባ ካርድ ለመውስድ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ከአጠቃላይ የምርጫ ጣቢያዎች መካከል በ17 ሺህ ያህሉ ዲጂታል የመራጮች ምዝገባን ተደራሽ እንደሚሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ቀደም ሲል ማስታወቁ የሚታወስ ነው።