ቀጥታ፡

ረቂቅ አዋጁ የስፖርት እድገትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27 /2018(ኢዜአ)፦የፌዴራል ስፖርት ልማትና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ የስፖርት እድገትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ ገለጹ።

ቋሚ ኮሚቴው በፌዴራል ስፖርት ልማት እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅን ለማዳበር የሚያስችል የውይይት መድረክ ከባለድርሻ አካላት ጋር አካሂዷል።


 

‎የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካ፤ የስፖርት ዘርፉ የሚመራበት ሁሉን አቀፍ የአሰራር ስርዓትና ህግ አለመኖሩን አንስተዋል።

የለውጡ መንግስት ይህን ችግር ለመፍታት የፌዴራል ስፖርት ልማት እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቷል ብለዋል።

ይህም ጠንካራ፣ ብቁና ጤናማ ትውልድን ለማፍራት፣ ስፖርት ከዜጎች የኑሮ ዘይቤ ጋር የተሳሰረ እንዲሆን አቅም እንዲፈጠር የሚያደርግ ነውም ብለዋል።

መንግስት ባለፉት ስምንት ዓመታት የዘርፉን ስብራት ለማከም በከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ በርካታ ተግባራትን ማከናወኑን ጠቁመው፤ በዚህም ከ17 ሺህ በላይ አነስተኛና መካከለኛ ስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራ በመላ ሀገሪቷ መገንባት መቻሉን ገልጸዋል።


 

ረቂቅ አዋጁ ስፖርት በተጠናከረ ህግና ስርዓት እንዲመራ በማድረግ የዘርፉን እድገት ለማፋጠን አቅም የሚፈጥር ነውም ሲሉ ሚኒስትሯ አክለዋል።

በመድረኩ ላይ የተሳተፉ የዘርፉ ተዋናዮች የረቂቅ አዋጁ መዘጋጀት በሀገሪቱ የስፖርት ዘርፉ ውጤታማ እንዳይሆን ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን ለመፍታት የሚያስችል እንደሆነ ገልጸው፤ ቢስተካከሉ ያሏቸውን ሀሳቦች አንስተዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ረቂቅ አዋጁ መዘጋጀቱ ለዘርፉ እድገት አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑን አንስተዋል።

በረቂቅ አዋጁ ፌዴሬሽኖች ደረጃውን የጠበቀ የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራ ይገነባሉ የሚል ድንጋጌ መኖሩን ጠቁመው፤ ይህ የፌዴሬሽኖችን አቅም ታሳቢ ያደረገ መሆኑን መፈተሽ ያስፈልጋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ በበኩላቸው፤ ረቂቅ አዋጁ ፍሬያማ ለማድረግ ከዓለም  አቀፍ የስፖርት ህጎች ጋር በተናበበ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ምክረ ሀሳብ ሰጥተዋል።

አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ ረቂቅ አዋጁ እንደ ሀገር በስፖርት ዘርፉ ላይ የሚፈለገውን ውጤት ለማመጣት ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር በኩል ጉልህ አበርክቶ ይኖረዋል ብሏል።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና፣ ማህበራዊ ልማት፣ ባህልና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወርቀሰሙ ማሞ ቋሚ ኮሚቴው የፌዴራል ስፖርት ልማት እና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ የተደራጀ እንዲሆን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ግብዓት ሲያሰባስብ መቆየቱን ገልጸዋል።

የፌዴራል ስፖርት ልማትና አስተዳደር ረቂቅ አዋጅ የስፖርት እድገትን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ምቹ ሁኔታ በመፍጠር በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም