በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ መስጠት የሚያስችለንን የምርጫ ካርድ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል - የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ድምጽ መስጠት የሚያስችለንን የምርጫ ካርድ ለመውሰድ ተዘጋጅተናል - የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፦ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ የመምረጥ መብታቸውን በመጠቀም ድምጽ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች አስታወቁ።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ግንቦት 24/2018 ዓ.ም ድምፅ በሚሰጥበት የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ከነገ ጀምሮ ይካሄዳል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች እንዳሉት፤ ምርጫ ዜጎች በሀገራቸው የዴሞክራሲ ባህል ግንባታ ላይ ንቁ ተሳትፎ የሚያደርጉበት የአደባባይ መድረክ ነው ብለዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫም ዴሞክራሲያዊ የመምረጥ መብታቸውን መጠቀም የምርጫ ካርድ በመውሰድ ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
አስራት ወልደሚካኤል እንደገለጹትም፤ ምርጫ ዜጎች የመምረጥና መመረጥ ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን የሚያስከብሩበት የዴሞክራሲ ሥርዓት መገንቢያ መሳሪያ ነው።
በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም ለኢትዮጵያ ዕድገትና ለህዝቦች ተጠቃሚነት ለሚሰራ የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የዲጂታል ቴክኖሎጂ የምርጫ ምኅዳር መፈጠሩም ጥራት ያለው የምርጫ ድምፅ አሰጣጥ ሥርዓት ወሳኝ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል።
በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ የሚሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመገናኛ ብዙኅን የሚያቀርቡት የክርክር መድረክም ዜጎች ይበጀኛል ለሚሉት ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት እንደሚያስችል አንስተዋል።
ሌላኛዋ አስትያየት ሰጪ ዘነበች አተው በበኩላቸው፤ የመምረጥና መመረጥ መብት በሕገመንግስቱ ለዜጎች የተሰጠ ዴሞክራሲያዊ መብት ነው ብለዋል።
ለዚህም በዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ላይ ድምፅ መስጠት የሚያስችላቸውን የምርጫ ካርድ በመውሰድ ሀገርን ወደተሻለ ምዕራፍ ያሻግራል ለሚሉት የፖለቲካ ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ምርጫ ዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን የሚጠቀሙበት የአደባባይ መድረክ ነው ያሉት ደግሞ የሻረግ በሽር ናቸው።
በዚህም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ነገ በሚጀመረው የመራጮች ምዝገባ የድምፅ መስጫ የምርጫ ካርድ ለመውሰድ መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሬድዮና ቴሌቪዥን የሚያደርጉት የምርጫ ቅስቀሳና የክርክር መድረክ መራጮች የሚሆናቸውን ለመምረጥ ግንዛቤ እየፈጠሩ መሆኑን አንሰተዋል።
እንደወጣት ጌታቸው ፀጋዬ ገለፃም፤ በነገው ዕለት በሚጀመረው የመራጮች ምዝገባ ላይ ድምፅ መስጫ ካርድ እንደሚወስድ አስታውቋል።
በምርጫ ወቅት የአንድ ሰው ድምፅ ትልቅ ዋጋ አለው ያለው ወጣት ጌታቸው፤ ለዚህም ዴሞክራሲያዊ መብቱን ለመጠቀም ድምፅ መስጫ ካርድ እንደሚወስድ ገልጿል።