ሴቶች በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ሴቶች በምርጫው በንቃት በመሳተፍ ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሚናቸውን ሊወጡ ይገባል
ደሴ፤ የካቲት 27/2018 (ኢዜአ)፡-ሴቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዛህራ ሑመድ አስገነዘቡ።
የዘንድሮ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን "50 ዓመት የሴቶች ድምጽ ለእኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ" በሚል መሪ ሀሳብ በወሎ ዩኒቨርሲቲ በፓናል ውይይት ተከብሯል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዛህራ ሑመድ በወቅቱ አንደገለጹት፣ የሴቶችን ሁለተናዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ በማሳደግ የኢትዮጵያን ሁለተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።
ሴቶች በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ለዲሞክራሲ ስርአት ግንባታ የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ለሀገር ዘላቂ ሰላምና ልማትም ሚናቸውን የበለጠ እንዲወጡ አሳስበዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሴቶችን የመሪነት እና የውሳኔ ሰጭነት ሚና ለማሳደግ በተደረገው ጥረት አበረታች ውጤት መመዝገቡን የተናገሩት ምክትል አፈ ጉባኤዋ፣ በምርጫው በመምረጥና በመመረጥ ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ሊያጎለብቱ ይገባል ብለዋል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ በበኩላቸው፣ በክልሉ የሴቶችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማሳደግ እየተደረገ ያለው ጥረት ውጤት እያስመዘገበ ነው ብለዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫም ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ በየደረጃው እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፣ ሴቶች ይበጀናል ያሉትን በመምረጥ ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙ አስገንዝበዋል።
ምርጫው ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ነጻ እንዲሆን በየደረጃው የየድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ የሶሾሎጂ መመህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ፋጡማ አብዱ በበኩላቸው፣ የሴቶች ሁለተናዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ እንዲያድግ አንድነታችንን ጠብቀን እንሰራለን ብለዋል።
በውይይቱ የፌዴራል፣ የክልል፣ የወሎ የኒቨርሲቲና የደሴ ከተማ አመራሮችን ጨምሮ ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።