ቀጥታ፡

ሴት የዩኒቨርሲቲ ምሁራን በሀገሪቱ የጾታ እኩልነት እንዲከበር ያበረከቱት አስተዋጽኦ ጉልህ ነው

ጎንደር፤ የካቲት 27/2018 (ኢዜአ)፡- ሴት የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ትውልድን ከመቅረጽ ባሻገር በሀገሪቱ የጾታ እኩልነት እንዲከበር ያበረከቱት አስተዋጽኦ ጉልህ ነው ሲሉ  የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ከይረዲን ገለጹ፡፡

የጎንደር ዩኒቨርሰቲ 50 አመት የሴቶች ድምጽ ለእኩልነትና ለበለጸገች ኢትዮጵያ በሚል መሪ ሀሳብ ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን በፓናል ውይይት አክብሯል፡፡ 


 

በመድረኩ ላይ የተገኙት ሚኒስትር ዴኤታዋ  ሴት ምሁራን  በእውቀት የዳበረ ትውልድን በመቅረጽ ረገድ  በትምህርቱ ዘርፍ ገንቢ ተግባራትን አከናውነዋል፡፡ 

ሴት ምሁራን የሴቶች እኩልነትና መብቶች እንዲከበሩ ግንባር ቀደም ሚና መጫወታቸውን ጠቁመው በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡

በሀገሪቱ በምርምሩ ዘርፍ የላቀ አበርክቶ ያላቸው የሴት ምሁራን ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ  መምጣቱን ተናግረዋል።

በሀገር ግንባታው ዘርፍ የሴት ምሁራን ተሳትፎ  የላቀ ሚና እንዳለው አመልክተው የሴት ምሁራን የሴቶችን ችግር በመፍታት ረገድ ተሳትፏቸው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡


 

የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዝዳንት  ካሳሁን ተገኝ (ዶ/ር) ሴቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለሰው ልጆች እኩልነት፣  ለፍትህ፣  ለዴሞክራሲና ለሰላም ያበረከቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ሴቶችን በትምህርት ከማብቃት ጀምሮ በምርምርና በሃላፊነት የሙያ ደረጃዎች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል ስርአት ዘርግቶ ለተግባራዊነቱ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ሴቶች በሳይንስና ቴክኖሎጂ አንዲሁም በአዳዲስ ፈጠራና ግኝቶች ዙሪያ እውቀታቸውንና ክህሎታቸውን ከፍ የሚያደርጉ የፖሊሲ አቅጣጫዎችን በመከተል ፍሬያማና ውጤታማ እንዲሆኑ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡


 

ሴት ምሁራን ችግር ፈቺ የምርምር ስራዎችን በማከናወን ሴቶች እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበትን አውድ መፍጠር አለባቸው ያሉት  ደግሞ የአማራ ክልል ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ብርቱካን ሲሳይ ናቸው፡፡

መንግስት ሴቶች በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካው ዘርፍ እኩል ተሳታፊና ተጠቃሚ አንዲሆኑ አስቻይ ሁኔታዎችን በመፍጠር ረገድ አበረታች ውጤት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።


 

በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሴት መምህራን ተመራማሪዎች ማህበር ፕሬዝዳንት የዝቤ ካሳ (ዶ/ር ) ማህበሩ ሴት ተማሪዎችን በማብቃት በተሰማሩበት መስክ ውጤታማና ስኬታማ እንዲሆኑ የድርሻውን እያበረከተ ይገኛል ብለዋል፡፡ 

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ115ኛ ጊዜ በሀገራችን ደግሞ  ለ50ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን አስመልክቶ  ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀው የፓናል ውይይት ላይ የዩኒቨርሲቲው ሴት ምሁራንን ጨምሮ  የፌደራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ተሳትፈዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም