በክልሉ በመሬት አስተዳደር ዘርፍ ህገወጥነትን ለመከላከል በተሰራ ሥራ ከ10 ሺህ በላይ የመሬት ይዞታዎች ህጋዊ ተደርገዋል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በመሬት አስተዳደር ዘርፍ ህገወጥነትን ለመከላከል በተሰራ ሥራ ከ10 ሺህ በላይ የመሬት ይዞታዎች ህጋዊ ተደርገዋል
ወላይታ ሶዶ፤የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፡-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በመሬት አስተዳደር ዘርፍ የሚስተዋሉ ህገ ወጥነቶችን ለመከላከል በተሰራ ሥራ ከ10 ሺህ በላይ ይዞታዎችን ህጋዊ ማድረግ መቻሉ ተገለጸ።
የክልሉ መሬት አስተዳደር ቢሮ በከተሞች ማስፋፊያ አካባቢ በጊዜያዊ የመሬት መጠቀሚያ ሠርተፊኬት አሰጣጥ፣ በህገ ወጥ የመሬት ወረራ እና ግንባታ መከላከል ላይ ያተኮረ የአቅም ማሳደጊያ መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ አካሂዷል።
የቢሮው ምክትልና የመሬት ይዞታ መረጃና ምዝገባ ዘርፍ ኃላፊ ዳንኤል ዳሌ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት ቢሮው ከተቋቋመ ጀምሮ በመሬት ዘርፍ የሚስተዋሉ ህገ ወጥነቶችን ለመከላከል ግብ ጥሎ እየሰራ ነው።
ለዚህም የባለሙያዎችን አቅም በማሳደግ የህግ ማዕቀፎችን መተግበር የሚያስችል አቅም መፈጠሩን ገልጸው፣ በማስፋፊያ አካባቢም ጊዜያዊ የመጠቀሚያ ሰርተፍኬት በመስጠት ህገ ወጥነትን ለመከላከል እየተሰራ ነው ብለዋል።
የመሬት ሀብት አስተዳደርን በሳይንሳዊ ዘዴ (በካዳስተር) በመምራት የመንግስትንና የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል።
በክልሉ የመሬት አስተዳደር ዘርፍ የሚስተዋሉ ማጭበርበሮችን ለመከላከል በተሰራው ሥራ እንደየመጠናቸው ከ53 ሺህ በላይ ህገወጥ ይዞታዎች መለየታቸውን የገለጹት ደግሞ የቢሮው ምክትልና የመሬት ልማትና አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ ኢንጂነር ፍሬው ፍሻለው ናቸው።
ከነዚህ መካከል 10 ሺህ ይዞታዎችን ህጋዊ ማድረግ መቻሉን ጠቁመው፣ ከህገ ወጦች የተወረሰ ከ29 ሄክታር በላይ መሬትም ወደ መሬት ባንክ እንዲገባ ተደርጓል ብለዋል።
ቢሮው ከተቋቋመ አጭር ጊዜ ቢሆነውም የተበታተኑ የአሰራር ስርዓቶችን ወደ አንድ የአሰራር ማዕቀፍ በማምጣት ዘርፉን ለማዘመን በተደረገ ጥረት ለውጥ እየታየ መምጣቱንም ጠቁመዋል።
ባለድርሻ አካላትም በመሬት ሀብት ቆጠራ፣ ምዝገባና መረጃን በማዘመን፣ ብልሹ አሰራሮችን በመከላከልና መልካም አስተዳደርን በማስፈን ላይ እንዲያተኩሩ አስገንዝበዋል።
በዘርፉ የሚስተዋለውን ሌብነትና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ተባብሮ መስራት በማስፈለጉ መድረኩ መዘጋጀቱንም ኢንጂነር ፍሬው ጠቁመዋል።
የወላይታ ዞን መሬት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ ታምራት በለጠ በበኩላቸው እንዳሉት በዘርፉ የሚስተዋሉ የአሰራር ብልሽቶች መንግስትን ከፍተኛ ሀብት ሲያሳጡ ቆይተዋል።
በዞኑ ሕገ ወጥ የመሬት ወረራ ለመከላከል በተደረገው ጥረት በአጭር ጊዜ ውስጥ 351 ሄክታር በላይ የገጠር መሬት ወደ ህጋዊ ቋት እንዲገባ መደረጉን ተናግረዋል።
በጋሞ ዞን መሬት አስተዳደር መምሪያ የመሬት ዝግጅትና መልሶ ማልማት ቡድን መሪ ቀሲስ ይታገሱ በቀለ በበኩላቸው እንዳሉት በዞኑ መሬትን ከህገ ወጦች ለመጠበቅ ግብረ ሃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ተገብቷል።
በዞኑ ባሉ አምስት ከተማ አስተዳደሮች በተደረገ ቁጥጥር በማስፋፊያ አካባቢዎች በህገ ወጥነት የተያዙ ከ5 ሺህ በላይ ይዞታዎች ህጋዊ ማድረግ መቻሉን ገልጸው፣ በቀጣይም ይሄ ሥራ ይጠናከራል ብለዋል።
ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው በዚህ መድረክ ላይ የክልል፣ የዞንና የከተማ አስተዳደር ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።