ቀጥታ፡

በከተማው ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የኢንዱስትሪ ዘርፉን አነቃቅቷል

ደብረ ማርቆስ፤ የካቲት 27/2018 (ኢዜአ)፡- በደብረ ማርቆስ ከተማ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የባለሀብቱን የማልማት ፍላጎት ከማነሳሳት ባለፈ የኢንዱስትሪ ዘርፉን ማነቃቃቱን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ።

በከተማው በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተከናወኑ ተግባራት በመስክ የተገበኙ ሲሆን የምክክር መድረክም ተካሄዷል።

የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ አቶ ተሾመ ዋለ በዚሁ ወቅት እንዳሉት የኢንዱስትሪ ዘርፉ ለከተማዋ ኢኮኖሚያዊ እድገት መነቃቃት ያለው አስተዋጾው የጎላ ነው።

በከተማዋ በርካታ ባለሃብቶች በኢንዱስትሪ ዘርፍ መሰማራተቸውን ገልጸው፤ በተሰማሩበት መስክ ውጤታማ እንዲሆኑም በመንግስት በኩል ጠንካራ ክትትልና እገዛ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በከተማዋ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የባለሃብቱን የማልማት ፍላጎት ከማነሳሳት ባለፈ የኢንዱስትሪ ዘርፉ እንዲነቃቃ በማድረግ በኩል የጎላ አበርክቶ እንዳለው ተናግረዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት መምሪያ ሃላፊ አቶ ተመስገን ተድላ በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ተቀዛቅዞ የነበረውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ እንዲነሳሳ አደርጓል።

የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከተጀመረ ወዲህ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት መጠን 20 በመቶ መጨመሩን እና ወደዘርፉ የሚሰማሩ ባለሀብቶች ቁጥር መበራከቱን ተናግረዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በዘርፉ የሚስተዋሉ የመሰረተ ልማት ችግሮችን ባለሃብቱን ባሳተፈ መንገድ መፍታት ተችሏል ብለዋል። 

በከተማው በዘርፉ ከተሰማሩ ከ250 በላይ ኢንዱስትሪዎች ከ90 በላይ የሚሆኑት ወደ ማምረት የገቡ ሲሆን ቀሪዎቹ በማሽን ተከላ ሂደት ላይ ናቸው ብለዋል።

በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩት ባለሃብቶች ከ33 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል ያስመዘገቡ መሆኑም ተገልጿል።

የመድረኩ መዘጋጀትም በማምረትም ሆነ በየደረጃው ያሉትን ፕሮጀክቶች ያለባቸውን ተግዳሮት በመለየት መፍትሄ ለማፈላለግና የከተማዋን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ ታሳቢ ያደረገ ነው።

በመድረኩ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና በኢንዱስትሪው ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም