ቀጥታ፡

ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጭነት ካርድ በመውሰድ ዴሞክራሲያዊ መብታችንን ለመጠቀም ተዘጋጅተናል - የመዲናዋ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፦ ለሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የመራጭነት ካርድ በመውሰድ ዴሞክራሲያዊና ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን ለመጠቀም ዝግጁ መሆናቸውን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል። 

ለዚህም የመራጮች ምዝገባ ነገ የካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች በይፋ ይጀመራል።

ኢዜአ በአዲስ ከተማና ጉለሌ ክፍለ ከተሞች ባደረገው የመስክ ቅኝት ለመራጮች ምዝገባ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁሶች ወደ ተለያዩ ወረዳዎችና ምርጫ ጣቢያዎች እየተጓጓዙ መሆኑን ተመልክቷል። 

የመዲናዋ ነዋሪዎች ምርጫው ለአገር ዕድገትና ለዜጎች ተጠቃሚነት ጉልህ ሚና ያለው በመሆኑ ቀድሞ ለመመዝገብና ለመምረጥ ዝግጁ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ 

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከልም አቶ ሞላ ስለሺ እንደገለጹት፤ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም የሚያስችላቸውን የመራጭነት ካርድ ለመውሰድ ተዘጋጅተዋል፡፡

በዚህም በመጪው ግንቦት ወር በሚካሔደው ጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን ለመጠቀም መዘጋጀታቸውንም ነው የገለጹት፡፡ 


 

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ብርሃኑ ጣሰው በበኩላቸው የሀገርን ልማትና ዕድገት ይበጃል ያሉትን የፖለቲካ ፓርቲ ለመምረጥ ግንባር ቀደም ተመዝጋቢና መራጭ እንደሚሆኑ ገልጸዋል። 

በተለይም በመገናኛ ብዙኃን የሚደረጉ ክርክሮች የተሻለ አማራጭ ሐሳብ ያላቸውን ፓርቲዎች ለመለየት እንደሚረዷቸው ጠቁመዋል።

ወጣት ኢሳ ሰሂድ ምርጫ ለአንድ አገር መሠረት፣ ለሕዝቦች አንድነትና የጋራ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን በመጥቀስ፤ የተሻለ ነገን ይፈጥራል የሚሉትን ለመምረጥ በንቃት እንደሚሳተፍ አስታውቋል።


 

በነገው ዕለት በሚጀመረው ምዝገባ የመራጭነት ካርድ ለመውሰድ መጓጓቷን የገለጸችው ወጣት ራሔል ገዛህኝ በበኩሏ፤ ምርጫ ይበጀኛል ለምለው ፓርቲ ድምፅ ለመስጠት የሚያስችለኝ ሕግ መንግስታዊ መብት በመሆኑ ይህንን ዕድል ለመጠቀም ዝግጁ ነኝ ብላለች፡፡ 


 

አስተያየት ሰጪዎቹ ምርጫው ለአገር ዕድገትና ለዜጎች ተጠቃሚነት ያለውን የጎላ ሚና በመረዳት ነገ በሚጀምረው የመራጮች ምዝገባ ላይ በንቃት ለመሳተፍ በከፍተኛ ተነሳሽነት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም