ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋት መርሀ ግብር የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አስችሏል

ጎንደር፤ የካቲት 27/2018 (ኢዜአ) ፡- የሌማት ትሩፋት መርሀግብር  የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ አስችሏል ሲሉ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂክማ ከይረዲን ገለጹ። 

50 አመት የሴቶች ድምጽ ለእኩልነትና ለበጸገች ኢትዮጵያ በሚል መሪ ሀሳብ የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ በጎንደር ከተማ ስኬታማ የሆኑ ሴቶች የልማት ተሳትፎ የመስክ ጉብኝት ተካሂዷል።  


 

ሚኒስትር ድኤታዋ በጉብኝቱ ላይ በሰጡት መግለጫ የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደ ሀገር የተነደፉ ስትራቴጂዎች ውጤታማነታቸው ከፍተኛ ነው። 

የሌማት ትሩፋት መርሀግብር  የሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅም በመገንባት  ሀብት አፍርተው ወደ ባለሀብትነት የሚሸጋገሩበትን እድሎች መፍጠሩን ተናግረዋል።  

በዚህም በርካታ ሴት ባለሀብቶችን በመፍጠር ምርታቸውን ከሀገር ውስጥ ባለፈ ለውጭ ገበያ በማቅረብ  በሀገር ኢኮኖሚ ግንባታ ውስጥ አሻራቸውን  ማሳረፍ እንደቻሉ አመልክተዋል። 

በክልሎች በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ የተጀመረው የሴቶች የልማት ህብረትም እንደ ሀገር ሞዴል እየሆነ መምጣቱን ጠቁመዋል።   

በጎንደር ከተማም በተቀናጀ የግብርና ልማት እንዲሁም በሴቶች የልማት ህብረት ሴቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገባቸውን ጠቅስዋል።


 

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ብርቱካን ሲሳይ  በክልሉ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶችን ህይወት ለመቀየር የተከናወኑ ተግባራት ተጨባጭ ውጤት አምጥተዋል።    

እለቱን ምክንያት በማድረግ የተካሄደው የመስክ ጉብኝት ውጤታማ የሆኑ ሴቶችን ተሞክሮ ለማስተዋወቅና ለማበረታታት ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።   

በጎንደር ከተማ በሌማት ትሩፋት መርሀግብር በመሳተፍ በ59 ዶሮ የጀመሩት የዶሮ እርባታ አሁን ላይ 47ሺ ማድረስ እንደቻሉ የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ ጽላተማርይ ተመስገን ናቸው። 


 

ከዶሮ እርባታ በተጨማሪ በንብ ማነብና በኩሬ አሳ  እርባታ መሰማራታቸውን ጠቁመው  የእንቁላልና የማር ምርት ለዉጪ ገበያ ማቅረብ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

በተሰማሩባቸው መስኮች ለ136 ሰዎች የስራ እድል መፍጠራቸውንም ገልጸዋል። 

በከተማው በተቀናጀ የወተት ሀብት ልማት የተሰማሩት ወይዘሮ  ሰብለ ማሩ  በ15ሺ ብር ካፒታል የጀመሩት  የወተት ልማት ስራ አሁን ላይ 80 የወተት ላሞች ባለቤት በመሆን ካፒታላቸውን 12 ሚሊዮን ብር ማድረስ ችለዋል።   

ለ50 ሰው የስራ እድል በመፍጠር በየቀኑ  500 ሊትር ወተት ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንደሆኑ ተናግረዋል።   

እለቱን ምክንያት በማድረግ በሴት ነጋዴዎች የተዘጋጀ  ባዛር ተመርቆ ተከፍቷል።

በጉብኝቱ ላይ የፌደራልና የክልሉ እንዲሁም  የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው ሴቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም