ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መብትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ምዕራፍ በመሆኑ ዜጎች የነቃ ተሣትፎ እንዲያደርጉ የበኩላችንን እንወጣለን - የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች - ኢዜአ አማርኛ
ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መብትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ምዕራፍ በመሆኑ ዜጎች የነቃ ተሣትፎ እንዲያደርጉ የበኩላችንን እንወጣለን - የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች
አዲስ አበባ፤ የካቲት 27 /2018(ኢዜአ)፦ ምርጫ ዴሞክራሲያዊ መብትን ለማረጋገጥ ወሳኝ ምዕራፍ በመሆኑ ዜጎች በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የነቃ ተሣትፎ እንዲያደርጉ የበኩላቸውን እንደሚወጡ የተለያዩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የዘንድሮው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም ይካሄዳል።
ለዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕጩዎች ምዝገባ የተከናወነ ሲሆን የመራጮች ምዝገባም ነገ የካቲት 28 ቀን 2018 በሁሉም የምርጫ ጣቢዎች ይጀመራል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ኃላፊዎች ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ለጠቅላላ ምርጫው ዴሞክራሲያዊነት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።
ምርጫ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ መሰረት በመሆኑ ዜጎች ይህንን አጋጣሚ በመጠቀም ነገ በሚጀመረው የመራጮች ምዝገባ የምርጫ ካርዳቸውን መውሰድ ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ የኮሙኒኬሽን ኃላፊ ነዋል አቡበከር፤ ከ180 በላይ ድርጅቶችን አቅፈው እንደሚንቀሳቀሱ ጠቅሰው፤ የህዝቡን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ስራዎችን እያከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
መራጮች በቂ እውቀት ኖሯቸው በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ እንዲሳተፉ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች ምርጫን በተመለከተ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የምርጫውን ተዓማኒነት ለማረጋገጥ ከ5 ሺህ በላይ ታዛቢዎችን ማዘጋጀታቸውን አክለው ታዛቢዎቹ በመላው አገሪቱ ተሰማርተው የምርጫውን ሂደት በቅርበት እንዲከታተሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ሁሉም ድርጅቶች ዜጎች ነገ በሚጀምረው የመራጮች ምዝገባ ላይ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡና ዴሞክራሲያዊ መብታቸውን እንዲጠቀሙም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ኅብረት ዳይሬክተር አቶ መሱድ ገበየሁ እንደገለጹት፤ ምርጫ ዜጎች ትልቅ የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያደርጉበትና ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱ የሚረጋገጥበት ሂደት ነው።
ኅብረቱ ሂደቱ ዴሞክራሲያዊ፣ ግልጽና ተዓማኒ በሆነ መልኩ እንዲጠናቀቅ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የምርጫ ሂደቱን ለመታዘብ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማጠናቀቃቸውንም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች የድርጊት መረብ ስራ አስኪያጅ አቶ አለሙ ኃይሌ በበኩላቸው ጥምረቱ በተለይ የአካል ጉዳተኞች በመራጭነትና በተመራጭነት ንቁ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
የአካል ጉዳተኞች በሁሉም ዘርፍ ያላቸው ተሳትፎ እንዲጎለብት በአገር አቀፍ ደረጃ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡