ቀጥታ፡

በክልሉ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ይጠናከራል

ደሴ፣ ደብረ ብርሃን ፤ የካቲት 27/2018-በአማራ ክልል የሴቶችን ሁለተናዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ ለማሳደግ የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተመላከተ።

50ኛውን ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን በማስመልከት በደብረ ብርሃንና በደሴ ከተሞች በሴቶች የተሰሩ የልማት ሥራዎች ተጎብኝተዋል።

በደብረ ብርሃን ዓለም አቀፉን የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ በተደረገው ጉብኝት ላይ የኢትዮጵያ ሴቶች ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት እና የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አየለች እሸቴ፤ የሴቶችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

በተለይም በተደራጀ አግባብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸውን ብሎም ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ወርቃለማሁ ኮስትሬ በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ ሴቶችን በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መስኮች እኩል ተጠቃሚና ተሳታፊ ለማድረግ እየሰራ ነው ብለዋል።

ወይዘሮ ኑኑሽ ዘነበ በበኩላቸው ሴቶች ተደራጅተው በሚሰማሩበት የስራ ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ እየተደረገ ያለው እገዛ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ገልጸዋል።

እርሳቸውም በአነስተኛ ካፒታል የጀመሩት የስራ ዘርፍ አሁን ላይ ከ1 ነጥብ አንድ ሚሊዮን ብር በላይ ማድረስ እንደቻሉም አመልክተዋል።


 

በተመሳሳይም በደሴ ከተማ በተካሄደው ጉብኝት ላይ የተገኙት በአማራ ክልል ሴቶች ህጻናት፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ንቅናቄ ተሳትፎና ማካተት ዳይሬክተር ወይዘሮ ደስታ ፈንታ፣ በክልሉ የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው።

በዚህም በአቅም ግንባታ ስልጠና፣ በገንዘብ ድጋፍ፣ በሥራ እድል ፈጠራና በሌሎችም ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የሴቶችን ተሳትፎ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።

ባለፉት ወራት ብቻ ከ18 ሺህ የሚበልጡ ሴቶችን በገቢ ማስገኛ ሥራ ላይ በማሰማራት በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።

ለዚህም በ578 ሚሊዮን ብር በጀት በእንሰሳት እርባታ፣ በግብርና፣ በሌማት ትርፋትና በሌሎችም ዘርፎች ተሰማርተው ለሌሎችም ሴቶች የሥራ እድል እንዲፈጥሩ ተደርጓል ብለዋል።

የደሴ ከተማ አስተዳደር ሴቶች፣ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ትግስት አበበ በበኩላቸው፣ ሴቶችን በእንስሳት እርባታና ማድለብ፣ በወተት ላም እርባታ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትና በሌሎች ዘርፎች እንዲሰማሩ ተደርጓል  ብለዋል። 

የደሴ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሰዓዳ አህመድ በሰጡት አስተያየት በሴቶች የልማት ሕብረት ተደራጅተው በተመቻቸላቸው መሬት የተለያዩ አትክልቶችን በማልማት ከቤት ፍጆታ አልፈው ለገበያ በማቅረብ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

መንግስት ባመቻቸልን የመስሪያ ሼድ ተደራጅተን እንጀራ በመጋገር ለምግብ ቤቶች፣ ለሆቴሎችና ለሌሎችም በማስረከብ ተጠቃሚ መሆን ችለናል ያሉት ደግሞ ወይዘሮ እርስቴ ካሳው ናቸው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም