የከተማውን ሰላምና ልማት በማስጠበቅ ረገድ የንግዱ ማህበረሰብ እያበረከተ ያለውን ሚና እንዲያጠናክር ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የከተማውን ሰላምና ልማት በማስጠበቅ ረገድ የንግዱ ማህበረሰብ እያበረከተ ያለውን ሚና እንዲያጠናክር ተጠየቀ
ባህር ዳር፤ የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፡- የባህር ዳር ከተማን ሰላምና ልማት በማስጠበቅ ረገድ የንግዱ ማህበረሰብ እያበረከተ ያለውን ሚና የበለጠ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባው የከተማ አስተዳደሩ አስገንዝቧል።
የከተማ አስተዳደሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በከተማዋ ከሚገኙ የንግድ ማህበረሰብ አባላት ጋር ውይይት አካሄዷል።
በውይይት መድረኩ ላይም የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ እንዳሉት የከተማውን ሰላምና ልማት በማስጠበቅ ረገድ የንግዱ ማህበረሰብ እያበረከተ ያለውን ሚና አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።
በከተማዋ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎች ሰፋፊ የህዝብን ተጠቃሚነት ሊያረጋግጡ የሚችሉ የልማት ስራዎች በስፋት እየተከናወኑና እየተፋጠኑ መሆኑን ገልጸዋል።
የንግድ ማህበረሰብም በከተማዋ እየተከናወኑ ባሉ የኮሪደርም ሆነ ሌሎች የልማት ስራዎች ላይ በንቃት እየተሳተፈ መሆኑን አውስተዋል።
በክልሉ አሁን ላይ የሰፈነውን ሰላም በማፅናት የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ የንግዱ ማህበረሰብ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
በመሆኑም ለከተማዋ ሰላምና ልማት መረጋገጥ እያበረከተ የሚገኘውን አስተዋፅኦ አጠናክሮ ሊያስቀጥል እንደሚገባም ምክትል ከንቲባው አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
የመድረኩ ተሳታፊ አቶ ጌጡ አንዳርጌ እንደገለጹት፤ የከተማውን ሰላምና ልማት በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ነጋዴው ማህበረሰብ በተደራጀ አግባብ እያደረገ ያለውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል።
ሌላኛዋ ተሳታፊ ወይዘሮ ዋጋ አዘዘ በበኩላቸው በከተማዋ ሰላምና ልማትን ለማረጋገጥ እየተደረገ ባለው ጥረት እየተወጣን የምንገኘውን ሚና እናጠናክራለን ብለዋል።
በመድረኩ በከተማው በተለያዩ የንግድ ዘርፎች የተሰማሩ ነጋዴዎችና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል።