በዞኑ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ይደረጋል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ አስፈላጊው ድጋፍና ክትትል ይደረጋል
አምቦ፤ የካቲት 27/2018 (ኢዜአ)፦ በምዕራብ ሸዋ ዞን እየተከናወኑ የሚገኙ የልማት ሥራዎች የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርጉ በዞኑ ምልከታ ያደረጉ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የጨፌ ኦሮሚያ አባላት ተናገሩ።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የጨፌ ኦሮሚያ አባላት በዞኑ በቶኬ ኩታዬ፣ በኢሉ ገላን እና በባኮ ወረዳዎች በኩታ ገጠም የለማ የሙዝ፣ የፓፓያ፣ የበጋ ስንዴና ሌሎች የልማት ሥራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።
አባላቱ ከጉብኝቱ በኋላ በዞኑ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት እንዲጠናከሩ የበኩላቸውን ድርሻ ለማበርከት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልና የዳኖ ምርጫ ክልል ተወካይ አለሙ ጎንፋ (ዶ/ር)፤ በዞኑ እየተከናወኑ ከሚገኙ የልማት ስራዎች በተለይም በግብርናና በሌሎች ልማቶች ላይ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎች ተስፋ ሰጪ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ሥራዎቹ በቴክኖሎጂ እንዲደገፉና አስፈላጊ ግብዓቶች እንዲሟሉላቸው ድጋፍ እና ክትትል በማድረግ የሀገሪቱን እድገት በማፋጠን ረገድ የራሳቸውን ድርሻ እንደሚወጡም ተናግረዋል።
ሌላዋ የጨፌ ኦሮሚያ አባልና የባኮ ምርጫ ክልል ተወካይ ወይዘሮ ኤቢሴ ፍርዲሳ በበኩላቸው፤ በዞኑ ከዚህ ቀደም ተሰርተው የማያውቁ ትላልቅ የልማት ሥራዎች መከናወናቸውንና ለሕብረተሰቡ የሥራ ዕድል መፈጠሩን መታዘባቸውን ገልጸው፣ ይህም የሀገሪቱን እድገት እንደሚያፋጥን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የሕዝብና የመንግሥት ሀብት ከሌብነትና ከብክነት በጸዳ መልኩ ለልማት እንዲውል አስፈላጊውን ክትትል እንደሚያደርጉና ሁሉም በዚህ ላይ እንዲሳተፍ መሥራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የጨፌ ኦሮሚያ አባላት ባደረጉት ጉብኝት ለሰጡት ገንቢ አስተያየት ያመሰገኑት የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አበበ ጨመዳ ናቸው።
የቀረቡትን ገንቢ ሐሳቦች በመጠቀም በዞኑ ከዚህ በላይ ያሉ የልማት ሥራዎችን በቴክኖሎጂ በመታገዝ በጥራትና በትኩረት ለመሥራት መታቀዱን ገልጸዋል።
በዞኑ የተሰሩ የልማት ሥራዎች አበረታች ቢሆኑም፣ ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከሕብረተሰቡ እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር ይጠናከራሉ ብለዋል።
በልማት ስራዎች የመስክ ምልከታው ላይ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የጨፌ ኦሮሚያ አባላትን ጨምሮ የዞኑ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።