ቀጥታ፡

በክልሉ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የኃይማኖት አባቶች ሚናቸውን ሊያጠናክሩ ይገባል-ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ

‎ባሀርዳር፤የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል በስነ-ምግባር የታነፀ ትውልድ በመገንባት ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የኃይማኖት አባቶች ሚናቸውን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለፁ።

‎"የመደመር መንግስት እና የኃይማኖት ተቋማት ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ ከወንጌላዊያን፣ ካቶሊክና ከ7ኛ ቀን አድቬንቲስት የሃይማኖት መሪዎች ጋር ክልላዊ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።


 

‎ርዕሰ መስተዳደሩ አቶ አረጋ ከበደ በመድረኩ ላይ እንደገለፁት፤ የኃይማኖት አባቶች የተረጋጋ ሀገረ መንግስት ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ሚናቸው ከፍተኛ ነው።

በተለይም ለተከታዮቻቸው ሰላምን በመስበክ፣ ትውልዱን በስነ-ምግባር በማነፅና በመገንባት ያላቸውን ሚና በተሻለ መንገድ መወጣት እንደሚገባቸው ነው የተናገሩት።

‎ኢትዮጵያ የብዝሃ ኃይማኖትና ቋንቋዎች ሀገር በመሆኗ ይህንን ጸጋ ለላቀ የሀገር ግንባታ ለማዋል በጋራ መስራት አሰፈላጊ በመሆኑ የውይይት መድረኩ መዘጋጀቱን ገልፀዋል። 

የኃይማኖት አባቶች በክልሉ ‎የሚስተዋሉ የሰላም ችግሮችን በዘላቂነት ለመቅረፍ፣ ሀገራዊ አንድነትን ለማጠናከር እና  ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት በሚከናወኑ ተግባራትም የተሻለ አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ነው ያመለከቱት።

የኃይማኖት አባቶች እስካሁን ለመጣው ሰላምና ልማት የጎላ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ጠቁመው በቀጣይም ይህንኑ አጠናክረው መቀጠል እንደሚጠበቅባቸው ነው ያሳሰቡት።

‎የክልሉ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ እሸቱ የሱፍ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኃይማኖት አባቶች ለሀገረ መንግስት ግንባታ የሚኖራቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ለሀገር ሰላምና ለትውልድ ግንባታ አበርክቷቸው ከፍተኛ በመሆኑም ሰላምን ለማጽናት በሚደረገው ጥረት ድርሻቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

በተለይም ገዥ ትርክት ላይ የተመሰረተ ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለመገንባት መንግስት እያደረገ ያለው ጥረት ስኬታማ እንዲሆንም ሚናቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

‎በሀገራዊና ህዝባዊ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ በተዘጋጀው መድረክ ላይ ከክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ የዕምነት አባቶችና የክልሉ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም