ባንግላዴሽ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና የኢንቨስትመንት ትብብር ለማጠናከር ትሻለች - አምባሳደር ሲትዋት ናየም - ኢዜአ አማርኛ
ባንግላዴሽ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድና የኢንቨስትመንት ትብብር ለማጠናከር ትሻለች - አምባሳደር ሲትዋት ናየም
አዲስ አበባ፤ የካቲት 27/2018(ኢዜአ)፦ ባንግላዴሽ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የንግድ እና የኢንቨስትመንት ትብብር ለማጎልበት ቁርጠኛ መሆኗን በኢትዮጵያ የባንግላዴሽ አምባሳደር ሲትዋት ናየም ገለጹ።
አምባሳደር ሲትዋት ናየም የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት በጣም ጥሩ በሚባል ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።
በተለይም ባንግላዴሽ እ.አ.አ በ2016 በኢትዮጵያ ኤምባሲ ከከፈተችበት ጊዜ አንስቶ ግንኙነቱ እየተጠናከረ መምጣቱን አመልክተዋል።
ሁለቱ ሀገራት የኢኮኖሚ ትብብራቸውን ለማሳደግ የጋራ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እንዳላቸውም አንስተዋል።
በቅርቡ የተካሄደው የባንግሌዴሽ እና የኢትዮጵያ የንግድ ትርኢት ሀገራቱ በዘርፉ ያላቸውን ትብብር ማጎልበት እንደሚቻል የታየበት ነው እንደነበርም ገልጸዋል።
በትርኢቱ የባንግላዴሽ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ላይ እንደሆነችና ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ እና በፍጆታ እቃዎች ላይ ፍላጎቷ እያደገ መምጣቱን ለመረዳት መቻላችውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ በጣም በፍጥነት እያደገችና የልማት ስራው አስደማሚ መሆኑን የገለጹት አምባሳደሩ ይህም ለባንግላዴሽ የንግድ ማህበረሰብ መልካም አጋጣሚ እንደሚፈጥር አመልክተዋል።
ሀገራቱ የንግድ ትብብራቸውን ማጠናከር ከሚችሉባቸው መስኮች አንዱ ቡና መሆኑንም አንስተዋል።
ኢትዮጵያ በቡና ወጪ ንግድ የምትታወቅ ሀገር መሆኗን ጠቁመው ባንግላዴሽ ቡናን ጠብቆ ማቆየት የሚያስችል ከተፈጥሮ ፋይበር(ቃጫ) የተሰራ ቦርሳ እንደምታመርትም ገልጸዋል።
ይህ በሀገራቱ ያሉ የንግድ ማህበረሰቦች ተቀራርበው እንዲሰሩና የዘርፉን ትብብር ለማጎልበት እንደሚያስችል ነው ያብራሩት።
ፋርማሲዩቲካልን ጨምሮ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ሌላኛው የትብብር አቅም እንደሆነም ጨምረው ተናግረዋል።
የባንግላዴሽ ባለሀብቶች ኢትዮጵያ ወደ አፍሪካ ሰፊ ገበያ መግቢያ በር መሆኗን በመገንዘብ መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱም ጥሪ አቅርበዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ለባንግላዴሽ ኢትዮጵያን ጨምሮ አጠቃላይ በአህጉሪቱ ያላትን የገበያ ተደራሽነት መጨመር የሚያስችሉ እድሎች እንዳሉትም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ እና ባንግላዴሽ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን የጀመሩት እ.አ.አ በ1976 መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።