ኢጋድ እና የአፍሪካ ኅብረት በሰላምና ደኅንነት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
ኢጋድ እና የአፍሪካ ኅብረት በሰላምና ደኅንነት ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር የጋራ ቁርጠኝነታቸውን ገለጹ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018 (ኢዜአ)፦ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን (ኢጋድ) እና የአፍሪካ ኅብረት በቀጣናው ሰላም እና ደኅንነት ያላቸውን ትስስር ይበልጥ ለማጎልበት እንደሚሰሩ አስታወቁ።
የኢጋድ የሰላም እና ደኅንነት ዘርፍ ዳይሬክተር ኮማንደር አበበ ሙሉነህ ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ጋር በኅብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ውይይት አድርገዋል።
ኮማንደር አበበ ሙሉነህ ውይይቱን ያደረጉት የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁን (ዶ/ር) በመወከል ነው።
ውይይቱ ኢጋድ እና የአፍሪካ ኅብረት በቀጣናው ሰላም፣ ደኅንነት እና መረጋጋት ላይ ያላቸውን የጋራ ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ነው።
ሁለቱ ወገኖች የጋራ የተግባር ምላሽ ለመስጠት እና ስትራቴጂካዊ ትብብራቸውን ለማጎልበት ቁርጠኛ እንደሆኑ መግለጻቸውን ኢዜአ ከኢጋድ ሴክሬተሪያት ያገኘው መረጃ ያመለክታል።