ቀጥታ፡

የመደጋገፍ እና የመረዳዳት እሴትን ለማጠናከር ሁሉም ማህበራዊ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ የመደጋገፍ እና የመረዳዳት እሴትን ለማጠናከር በሚከናወኑ ተግባራት ሁሉም ማህበራዊ ኃላፊነቱን ሊወጡ እንደሚገባ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ገለጹ።

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ጋር በመተባበር ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን ለመርዳት ያለመ "የረመዳን ሶሊዳሪቲ" የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡

ስምምነቱን የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ ፈርመውታል።

ሚኒስትሯ ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) በመርሃ-ግብሩ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ረመዳን የጾም፣ የጸሎትና የማካፈል ወር መሆኑን ጠቅሰዋል።

መንግስት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሰፋፊ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸው፤ ውስብስብ ጉዳዮችን በጋራ ለመፍታት የሁሉንም አካላት ተሳትፎ ይጠበቃል ብለዋል፡፡

ስምምነቱ ለረመዳን ወር ብቻ ተገድቦ የሚቀር ሳይሆን፤ ወደፊትም ሌሎች አካላትን በማካተት ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው ብለዋል።

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ በበኩላቸው፤ መተጋገዝ እና መረዳዳት የሰው ልጅ ግዴታ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።

መረዳዳት በጎ ተግባር መሆኑን ገልጸው፤ ሚኒስቴሩ ያቀረበው ሃሳብ መልካም ዓላማ ያለው በመሆኑ ሁሉም ዜጋ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

ይህ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ-ግብር በዋናነት ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በዘላቂነት መደገፍ፣ የአብሮነት እና የመረዳዳት እሴትን ማጠናከር እንዲሁም ለጋራ ዓላማ በጋራ መቆም እንደሚቻል በተግባር ማሳየትን ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም