በአፋር ክልል በመስኖ ልማት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች ናቸው - ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በአፋር ክልል በመስኖ ልማት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች ናቸው - ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር)
ሰመራ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል በመስኖ ልማት ላይ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን የመስኖና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ በክልሉ እየተከናወኑ ያሉ የመስኖ ልማት ስራዎችን ፤ግድብና የእንስሳት መኖ ልማት ስራን ተመልክተዋል።
ሚኒስትር አብርሃም በላይ (ዶ/ር) በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለጹት፤ በአፋር ክልል የመስኖ ስራዎችን በማጠናከር ረገድ የሚከናወኑ ተግባራት የሚበረታቱ ናቸው።
በተለይም በዱብቲ ወረዳ በማህበር ተደራጅተው በፍራፍሬና አትክልት ልማት የተሰማሩ ወጣቶች እያከናወኑት ያለው ስራ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።
የዱብቲ ወረዳ የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ሙባረክ መሐመድ፣ በወረዳው በሁለት ማህበር የተደራጁ ወጣቶች ወደ ስራ ገብተዋል ብለዋል።
ማህበራቱ በ14 ሄክታር መሬት ላይ ፓፓያ፣ ሙዝ፣ ማንጎ፣ ብርቱካን፣ ሎሚና ቴምር በማልማት ላይ መሆናቸውን አብራርተዋል።
የመስኖ ስራዎችን በማጠናከር ወጣቶች ወደ ስራ እንዲገቡ ከማድረግ አኳያ በሚኒስቴሩ ስር የሚገኘው የቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
የቆላማ አካባቢ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት በአፋር ክልል በ5 ክላስተርና በ23 ወረዳዎች ላይ የተለያዩ የልማት ስራዎችን በማከናወን፣ ለአርብቶ አደሩ ኑሮ መሻሻል ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑም ተመልክቷል።
በጉብኝት መርሃ ግብሩ ላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የአፋር ክልል ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተሳትፈዋል።