የኢትዮጵያን ዲጂታል መሠረተ-ልማት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ስምምነት ተፈረመ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ዲጂታል መሠረተ-ልማት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ስምምነት ተፈረመ
አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮ ቴሌኮም የኔትወርክ ማስፋፊያን በማከናወን እና በማዘመን የኢትዮጵያን ዲጂታል መሠረተ-ልማት ወደ ላቀ ደረጃ ማሸጋገር የሚያስችል ታሪካዊ ስምምነት ከኤሪክሰን ኩባንያ ጋር ተፈራረመ።
ስምምነቱ በኤሪክሰን የኔትወርክ አሥተዳደር ቀጣና ውስጥ በሚገኙ 1 ሺህ 500 የሞባይል ጣቢያዎች ላይ የማስፋፊያ፣ የማሻሻያ፣ የ4ጂ ንጣፍ እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የመገንባት ሥራዎችን ያካትታል ተብሏል።
ይህ ሁለንተናዊ የማዘመን ኢኒሼቲቭ የኔትወርክ ሽፋንን፣ ጥራትንና ዐቅምን በከፍተኛ ሁኔታ የሚያሻሽል መሆኑን የኢትዮ ቴሌኮም መረጃ አመላክቷል።
በዚህም ነባር መሠረተ ልማቶችን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በመተካት፤ የ4ጂ ሽፋን እና ዐቅምን በከፍተኛ ደረጃ የሚያሳድግ መሆኑ ተጠቁሟል።
የ5ጂ ተደራሽነትንም በማስፋት ለዘመናዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ የሚያስፈልገውን ከፍተኛ የፍጥነት ኮኔክቲቪቲ ዕውን ለማድረግ ያስችላል ነው የተባለው።
በተለይም ፕሮጀክቱ 75 ለሚሆኑ የገጠር አካባቢዎች ተስማሚ የሆኑ የሞባይል ቴክኖሎጂ ሶሉሽኖችን ለማቅረብ እንደሚያስችልም ተመላክቷል።
በተጨማሪም 502 ነባር የ3ጂ ጣቢያዎችን ለማዘመን እና ወደ ላቀ የ4ጂ ቴክኖሎጂዎች ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል።
ፕሮጀክቱ በኤሪክሰን (Ericsson) የኦፕሬሽን ቀጣና ውስጥ 2 ነጥብ 8 ሚሊየን አዲስ የ4ጂ ኔትዎርክ የመሸከም ዐቅም ለመጨመር የሚያስችል ሲሆን፤ ይህም አጠቃላይ የኔትዎርክ ዐቅሙን ወደ 4 ነጥብ 1 ሚሊየን ለማድረስ ያስችላል ተብሏል።
በተጨማሪም የኤልቲኢ (LTE) አገልግሎትን ወደ 157 ተጨማሪ ከተሞች በማስፋፋት፣ አጠቃላይ የኤልቲኢ አገልግሎት ተጠቃሚ ከተሞችን ቁጥር ወደ 276 ያደርሳል ብሏል ኢትዮ ቴሌኮም።
ይህም ሽፋንን በ45 በመቶ በማሳደግ፤ በሪጂኑ ያለውን አጠቃላይ የሕዝብ ሽፋን 85 በመቶ ለማድረስ እንደሚያስችል ጠቁሟል።
ስምምነቱ የኢትዮጵያውያንን የአኗኗር ዘይቤ፣ አሠራር እና ግብይት የሚያከናውኑበትን መንገድ ወደ ላቀ ደረጃ እያሸጋገሩ የሚገኙ፤ እንደ ቴሌብር፣ ዘመን ገበያ እና ዘኔክሰስ ለመሳሰሉ ፕላትፎርሞች ድጋፍ ይሰጣል።