በክልሉ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የህዝብን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)
ሀደሮ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የሚተገበሩ የልማት ፕሮጀክቶች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ገለፁ፡፡
በክልሉ መንግሥት በጀት በከምባታ ዞን በተለያዩ መዋቅሮች ተገንብተው የተጠናቀቁ የመንገድ፣ የንፁህ መጠጥ ውሃና የመስኖ ፕሮጀክቶች በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት ሆነዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በክልሉ የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ፕሮጀክቶችን እውን ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት በቀጣይም ተጠናክረው ይቀጥላሉ።
የክልሉ መንግስት ለማህበረሰቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ ለመስጠት ከምንጊዜውም በላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
ዛሬ ተመርቀው ለአገልግሎት ክፍት የተደረጉት የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የመስኖ እና የመንገድ ፕሮጀክቶች የዚሁ አካል መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በክልሉ የትምህርት ቤት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና የኤሌክትሪክ ሀይል ተደራሽነትን ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት።
የክልሉ መንግስት በዞኑ ሀደሮ ጡንጦ ዙሪያ ወረዳ አንድ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በአጭር ጊዜ ውስጥ ገንብቶ እንደሚያስረክብም አረጋግጠዋል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሰረተ ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ መሀመድ ኑርዬ(ዶ/ር) እንዳሉት፣ በክልሉ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ጀምሮ የማጠናቀቅ ልምድ እየዳበረ መጥቷል ብለዋል፡፡
ማህበረሰቡ ዛሬ የተመረቁ ፕሮጀክቶችን በአግባቡ በመጠበቅ ለታለመላቸው ጥቅም እንዲውሉ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እንዲወጣም አስገንዝበዋል፡፡