ቀጥታ፡

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሕዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ተሳትፏቸውን የሚያጠናክሩበት አስቻይ ሁኔታ ተፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ የካቲት 26/2018(ኢዜአ)፦ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሕዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ተሳትፏቸውን የሚያጠናክሩበት አስቻይ ሁኔታ መፈጠሩን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚያካሂድና የመራጮች ምዝገባም ከየካቲት 28 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚካሄድ አስታውቋል።

ቦርዱ ጠቅላላ ምርጫውን ነፃ፣ ፍትሕዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በሚያደርገው ጥረት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፎ ወሳኝ ሚና አለው።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፋሲካው ሞላ ከኢዜአ ጋር ባደርጉት ቆይታ፤ ለጠቅላላ ምርጫ ዴሞክራሲያዊነት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ተሳትፎ ወሳኝ ነው ብለዋል።

በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ በታዛቢነት፣ በመራጮች ግንዛቤ መፍጠርና ሌሎች ተሳትፎዎች የሚኖራቸውን ሚና ለማጎልበት ከሚመከለታቸው ተቋማት ጋር ተቀራርበው እንዲሰሩ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ ነፃ፣ ፍትሕዊና ዴሞክራሲያዊነት ለማስጠበቅ በሚደረገው ጥረት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል።

በዚህም በጠቅላላ ምርጫው ላይ 45 በታዛቢነት፤ 169 በመራጮች ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ የሚሳተፉ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ፈቃድ እንደተሰጣቸው አስታውቀዋል።

በቀጣይም በምርጫ ሂደቱ በተለያየ መንገድ ተጨማሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ሊሳተፉ እንደሚችል አስረድተዋል።

በምርጫ ቦርድ በታዛቢነትና በመራጮች ትምህርት ፈቃድ የተሰጣቸው የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም አባላቶቻቸውን በመመልመል ስልጠና እየሰጡ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ለጠቅላላ ምርጫው አሳታፊነት፣ አካታችነት፣ ዲሞክራሲያዊነትም ለሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚደረጉ የድጋፍና ክትትል ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችም በተሰጣቸው የምርጫ ተሳትፎ ዕውቅና መሰረት ምርጫው ነፃ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ገንቢ ሚና መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም