በጂንካ ከተማ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የተሰማሩ ዜጎች ውጤታማ እየሆኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጂንካ ከተማ በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የተሰማሩ ዜጎች ውጤታማ እየሆኑ ነው
ጂንካ፤ የካቲት 26/2018 (ኢዜአ):-በጂንካ ከተማ አስተዳደር በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በወተት ልማትና በዶሮ እርባታ ሥራ የተሰማሩ ነዋሪዎች ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ተናገሩ።
በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና ስርዓተ ምግብን ለማሻሻል ወሳኝ ሚና ያለው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በየአካባቢው ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ ነው።
በጂንካ ከተማ በመርሀግብሩ እየተሳተፉ ያሉ ነዋሪዎችም ውጤታማ እየሆኑ መምጣታቸውን ለኢዜአ ተናግረዋል።
ከተጠቃሚዎቹ መካከል አቶ ገዛህኝ አዲሱ እንዳሉት በሁለት የወተት ላሞች በመኖሪያ ግቢያቸው የጀመሩት የእርባታ ሥራ ዛሬ ላይ እየተስፋፋ መምጣቱን ተናግረዋል።
በተለይም በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ለዘርፉ ትኩረት መሰጠቱ ለውጤታቸው አስተዋጾ ማድረጉን ገልጸው፣ የወተት ምርታቸውን ከቤት ውስጥ ፍጆታ ባለፈ በየቀኑ ከ40 ሊትር በላይ ወተት ለማህበረሰቡ በማቅረብ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በሥጋ ዶሮ እርባታ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ኡመር ጀማልም በግብርና ባለሙያዎች ታግዘው ምጥን መኖ በማዘጋጀት የሥጋ ዶሮዎችን እያረቡ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የዶሮ እርባታ አዋጭ ሥራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ኡመር፣ የ45 ቀን ጫጩቶችን ተረክበው በማሳደግና በስድስት ወራት ውስጥ ለሽያጭ በማቅረብ ትርፋማ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።
ወይዘሮ ሩሃማ እንግዳ በበኩላቸው ከሌሎች አካባቢዎች ባገኙት ተሞክሮ በመኖሪያ ግቢያቸው በዘመናዊ መልክ የአሣ ጫጩቶችን እያረቡ ይገኛሉ።
በአካባቢው የአሣ እርባታ ሥራ ባለመለመዱና አቅርቦቱም በቂ ባለመሆኑ ለስራው እንዳነሳሳቸው ገልጸው ባላቸው አነስተኛ ግቢ በ50 የአሣ ጫጩቶች ሥራውን መጀመራቸውን ተናግረዋል።
"በሙከራ ደረጃ የጀመርኩት የአሣ እርባታ ሥራ አሁን ላይ ውጤታማ እየሆነ በመምጣቱ ዓሣን በስፋት በማምረት ለገበያ ለማቅረብ አቅጂያለሁ" ብለዋል።
በጂንካ ከተማ አስተዳደር የግብርና ዩኒት አስተባባሪ አቶ አይናለም ጨነቀ እንዳሉት በከተማው የዶሮ፣ የሥጋ፣ የወተት፣ የማርና የዓሣ መንደር በመመስረት ከ8ሺህ 700 በላይ ተጠቃሚዎች በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር እንዲሳተፉ ተደርጓል።
የሌማት ትሩፋት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ በከተማው በወተት፣ በዕንቁላል፣ በዶሮና በማር አቅርቦት መሻሻል እንዲመጣ አድርጓል ብለዋል።
ለነዋሪዎቹ የተሻሻሉ ዶሮዎች፣ የወተት ላሞችና የአሣ ዝርያዎችን በማቅረብ ተጠቃሚ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።
ነዋሪዎቹ በተጨማሪም አትክልትና ፍራፍሬዎችን በዘመናዊ መልክ በማልማትና በመጠቀም የአመጋገብ ስርአታቸውን እንዲያሻሽሉ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን አንስተዋል።
ከግለሰቦች በተጨማሪ የተለያዩ ተቋማት በሌማት ትሩፋት መርሀግብር በመሳተፍ የውስጥ ገቢያቸውን ከማሳደግ ባለፈ ለአካባቢው ማህበረሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ ምርት በማቅረብ እያገዙ መሆናቸውን ጠቁመዋል።