ቀጥታ፡

ማዕከሉ በተቋቋመ ስድስት ወራት ውስጥ ከ23 ሺህ በላይ ሰዎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት አግኝተዋል

ድሬደዋ፣ የካቲት 26/2018(ኢዜአ) :-የድሬዳዋ መሶብ የአንድ ማዕከል በተቋቋመ ስድስት ወራት ውስጥ ከ23 ሺህ በላይ ሰዎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸው ተገለጸ።

የማዕከሉ አስተባባሪ አቶ አወቀ ለገሰ ለኢዜአ እንደገለጹት በመስከረም 2018 ስራ የጀመረው ማእከሉ  በ10 ተቋማት 28 አገልግሎቶች እየተሰጡ ነው።

ማእከሉ ስራ ከጀመረ ወዲህ ከ23ሺህ በላይ ሰዎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።


 

ማእከሉ ከወረቀት ንክኪ የፀዳ ዘመናዊ፣ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት የህዝብ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መፍታት እያስቻለ መሆኑን ተናግረዋል።

በተሰራው የእርካታ ዳሰሳ ጥናት ህብረተሰቡ በመንግስት አገልግሎት ከፍተኛ እርካታ ማግኘት እንደቻለ መረጋገጡን አመልክተዋል።

በማዕከሉ የተሰባሰቡ ተቋማት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ ተገልጋዮች ናቸው።

ከተገልጋዮች መካከል አቶ አብዲ ቡሽራ እንዳሉት በማዕከሉ የሚሰጡት ዲጂታል አገልግሎቶች አስደሳች መሆናቸውን ገልጸዋል።


 

በማዕከሉ የይዞታ ካርታ ለማውጣት መጥተው ፈጣን አገልግሎት በማግኘታቸው ጉዳያቸውን በአጭር ጊዜ አጠናቀው ወደ ስራቸው መመለስ እንደቻሉ ተናግረዋል።

ቀደም ሲል ተቋማት በተለያዩ አካባቢዎች ተበታትነው ስለሚገኙ አንድ አገልግሎት ለማግኘት እስከ ሳምንት ጊዜ እንደሚፈጅና ብዙ ድካም ይጠይቅ እንደነበር አስታውሰው አሁን ላይ በመጣው ለውጥ መደሰታቸውን ገልጸዋል።


 

ወይዘሮ ሰላማዊት ሐጎስ በበኩላቸው ግብር ለመክፈል ወደ ማእከሉ መምጣታቸውን ጠቁመው  ጉዳያቸውን በአጭር ጊዜ መጨረሳቸውን ተናግረዋል ።

ወደ ማእከሉ ጉዳይ ለማስፈጸም መጥተው ፍትሃዊና ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘታቸውን የገለጹት ደግሞ አቶ ፍሰሐ ሰለሞን ናቸው።


 

በማእከሉ ተቋማት በሚሰጡት ፈጣን አገልግሎት መደሰታቸውን ጠቁመው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመልክተዋል።

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም